በዳንግላና አካባቢው የሚገኘው ጥምር ጦር የሰላም ማስከበር ተልዕኮውን በብቃት እየተወጣ መሆኑን ገለጸ።
በአዊ ብሄረሰብ አስተዳደር የዳንግላ ከተማና አካባቢዋን ሰላምና ደህንነት ለማረጋገጥ የተሰማራው ጥምር ጦር፣ የተሰጡትን ግዳጆች በላቀ ብቃትና በቁርጠኝነት እየተወጣ እንደሚገኝ አስታውቋል።
በዳንግላ ዙሪያ ወረዳ ፖሊስ ፅህፈት ቤት የእስረኛ አቀራረብ ንዑስ ክፍል ኃላፊ ምክትል ኢንስፔክተር ሀሰን አህመድ እንደገለጹት፤ ፖሊስ ከሰላም አስከባሪ፣ ከሚሊሻ እና ከፌዴራል የጸጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት የተሰጠውን ግዳጅ በስኬት እየተወጣ ነው።
ፖሊስ ከመደበኛ የወንጀል መከላከል ተግባሩ ባሻገር፣ ወቅታዊውን የህግ ማስከበር ተልዕኮ እንደ ድርብ ኃላፊነት ወስዶ እየሰራ ይገኛል። ለህዝብ ሰላምና ለሀገር ደህንነት ሲባልም አስፈላጊውን መስዋዕትነት እየከፈልን ነው ሲሉ ምክትል ኢንስፔክተሩ አስረድተዋል።
በአካባቢው አስተማማኝ ሰላም እንዲሰፍንና የህዝብ ደህንነት እንዲጠበቅ ሌት ተቀን እየሰሩ እንደሚገኙም ጠቁመዋል።
በወረዳው ፖሊስ ፅህፈት ቤት የዕቅድ ዝግጅት ንዑስ ክፍል ኃላፊ ዋና ሳጂን በላይሰው አርጋው በበኩላቸው፣ በክልልም ሆነ በሀገር ደረጃ የተጋረጠውን የጸጥታ ችግር ለመቀልበስ ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል።
በሰላም እጦት ለተጎሳቆለው ማህበረሰብ ካሳ የሚሆን ሰላም ለማምጣት ያላቸው ቁርጠኝነት ከፍተኛ መሆኑንም አረጋግጠዋል።
የሰላም አስከባሪ አባል የሆኑት አቶ ብርሀኑ ገድፍ በበኩላቸው ጥምር ጦሩ እያከናወናቸው ያሉትን ተግባራት
በኬላዎች ላይ ጥብቅ ፍተሻ ማድረግ፤የሰርጎ ገብነት ሙከራዎችን ማክሸፍ፤ማንኛውንም አይነት ህገወጥነት መቆጣጠር እና የሰላም አማራጭን በማይቀበሉ ህገ-ወጥ አካላት ላይ የማያዳግም የህግ ማስከበር እርምጃ መውሰድ መቻሉን ገልጸዋል።
በመጨረሻም፣ የጥምር ጦሩ አባላት ሀገራዊ የእድገት ጉዞው እንዳይሰናከልና ህዝቡ የሰላም አየር እንዲተነፍስ እስከ መጨረሻው እንደሚታገሉ ቃል ገብተዋል።




