በዱርቤቴ ከተማ በህገ-ወጥ መንገድ ሲጓጓዝ የነበረ ናፍጣ በቁጥጥር ስር ዋለ።
በሰሜን ጎጃም ዞን ዱርቤቴ ከተማ በህገ-ወጥ መንገድ ሲጓጓዝ የነበረ 6,400 ሊትር ናፍጣ፣ በጸጥታ ሀይሉና በማህበረሰቡ የተቀናጀ ጥረት በቁጥጥር ስር መዋሉ ተገለጸ።
የሰሜን ጎጃም ዞን ፖሊስ መምሪያ አዛዥ ኮማንደር በሪሁን አየነው እንደገለጹት፣ ለዚህ ውጤት መገኘት የአካባቢው ማህበረሰብ የሰጠው ጥቆማና ትብብር ከፍተኛውን ድርሻ እንደሚይዝ ገልጸዋል።
ህብረተሰቡ የሀገር ሀብት በህገ-ወጦች ሲመዘበር ዝም ብሎ አለማየቱ ከጸጥታ ሀይሉ ጋር ያለውን ጠንካራ ቅንጅታዊ ስራ በተግባር ያሳየበት አጋጣሚ እንደሆነም ጠቁመዋል።
የተገኘው ውጤት የጸጥታ ሀይሉ የንቃት ደረጃና የህዝባችን ተባባሪነት ድምር ውጤት ነው ያሉት አዛዡ የጸጥታ ኃይሉ ከማህበረሰቡ የደረሰውን ጥቆማ በፍጥነት ወደ ተግባር በመቀየር በጥበብና በበሰለ የኦፕሬሽን ስራ እንቅስቃሴውን በመከታተል ያለ ምንም መዘግየት ህገ-ወጥ ድርጊቱን በቁጥጥር ስር በማዋል የሚደነቅ ሙያዊ ብቃት ማሳየቱን አብራርተዋል ።
ኮማንደር በሪሁን አየነው አክለውም፣ ህገ-ወጥ የንግድ እንቅስቃሴና ኮንትሮባንድ የሀገርን ኢኮኖሚ የሚጎዱ በመሆናቸው፣ እነዚህን ተግባራት በጋራ መከላከል የሁልጊዜም ተግባር ሊሆን እንደሚገባ አሳስበዋል።
የጸጥታ ሀይሉ እንዲህ አይነት የሀገርን ጸጋ የሚያሳጡ ህገ-ወጥ ተግባራትን ለመከላከል በሙሉ ዝግጁነትና በጠነከረ አቋም እንደሚሰራ ጠቁመው ለህገ-ወጦች ምንም አይነት ክፍተት አንሰጥም ሲሉም አረጋግጠዋል።
ህብረተሰቡ ለጸጥታ ኃይሉ አይንና ጆሮ በመሆን በዞኑ ለሚፈጸሙ ህገ-ወጥ ድርጊቶች ለሚሰጠው ጥቆማ እና ወንጀልን ለመከላከል እያሳየ ላለው ቁርጠኝነት በዞኑ ፖሊስ መምሪያ ስም ምስጋና አቅርበዋል ።
ህገ-ወጥ ነዳጁን ጭኖ ሲንቀሳቀስ የነበረው መኪና ኮድ አማ 3-B 73508 ሲሆን ከእነ ረዳቱ በቁጥጥር ስር ውሎ አስፈላጊው ምርመራ እየተጣራበት እንደሚገኝም አዛዡ ጠቁመዋል::


