በምዕራብ ጎንደር ዞን ሲንቀሳቀስ የነበረ የቅማንት ታጣቂ ቡድን አባላት በሰላም እጃቸውን ሰጡ
በምዕራብ ጎንደር ዞን ሲንቀሳቀስ የነበረ የቅማንት ፅንፈኛ ቡድን አባላት መንግስት ያቀረበውን የሰላም አማራጭ በመጠቀም በምህረት ወደ ሰላማዊ ህይወት መመለሳቸው ተገለጠ።
ቡድኑ በዛሬው ዕለት በቡድን በመሆን የያዘውን ትጥቅ ለመንግስት የጸጥታ አካላት አስረክቧል።
ታጣቂ ቡድኑ ላለፉት ጊዜያት በአካባቢው ሲንቀሳቀስ የቆየ ቢሆንም፣ ሰላምን በዘላቂነት ለማምጣትና በውይይት ችግሮችን ለመፍታት የቀረበለትን ጥሪ በመቀበል በምህረት ለመግባት መወሰኑ ተገልጿል። ይህም በዞኑ ያለውን አንጻራዊ ሰላም ይበልጥ እንደሚያጠናክረው ታምኖበታል።
በዚሁ የምህረት ሂደት ውስጥ የተሳተፉት 31 የሰው ኃይል ሲሆኑ፣ ይዘዋቸው የገቡት የጦር መሳሪያዎች ዝርዝርም 23 ክላሽንኮቭ (AK-47)፣ 1 ዲሽቃ፣ 1 ብሬን፣ 8 ጀሌ መሆኑ ተገልጿል።
እጃቸውን የሰጡት የቡድኑ አባላት አስፈላጊው የተሃድሶ ስልጠና እንደሚሰጣቸውና በቀጣይም ወደ ማህበረሰቡ ተቀላቅለው ሰላማዊ ህይወታቸውን እንዲመሩ ምቹ ሁኔታዎች እንደሚፈጠሩ ይጠበቃል።
ይህ እርምጃ በክልሉ ለሚታየው የሰላም ጥረት አዎንታዊ ተምሳሌት እንደሚሆንም የጸጥታ አካላት ጠቁመዋል።


