የፖሊስ ተቋምን ወደ ላቀ ከፍታ የሚያሸጋግሩ የቢሮ ግንባታዎችና ምቹ የስራ አካባቢን መፍጠር፣ ለላቀና ለተቀላጠፈ የህዝብ አገልግሎት ዋነኛ መሠረት መሆኑ ተገለጸ።

የፖሊስ ተቋምን ወደ ላቀ ከፍታ የሚያሸጋግሩ የቢሮ ግንባታዎችና ምቹ የስራ አካባቢን መፍጠር፣ ለላቀና ለተቀላጠፈ የህዝብ አገልግሎት ዋነኛ መሠረት መሆኑ ተገለጸ።

የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ የጀመረውን ተቋማዊ የሪፎርም ጉዞ ለማፋጠንና ለህብረተሰቡ የሚሰጠውን አገልግሎት ይበልጥ ዘመናዊ ለማድረግ፣ የመሠረተ ልማት ግንባታዎች ወሳኝ ሚና እንደሚጫወቱ ተገልጿል።

የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ኮሚሽነር ጀነራል ዘላለም መንግስቴ (ዶ/ር)፣ የባህር ዳር ከተማ አስተዳደር ፖሊስ መምሪያ ከ4 ሺህ ካሬ ሜትር በላይ በሆነ ስፋት ላይ እያስገነባ ያለውን የቢሮ ህንፃ በቦታው ተገኝተው ጎብኝተዋል።

ኮሚሽነር ጀነራል ዘላለም መንግስቴ (ዶ/ር)

በጉብኝታቸው ወቅት እንደገለጹት፣ ይህ ግንባታ ተራ የቢሮ ህንፃ ብቻ ሳይሆን የክልሉ ፖሊስ የጀመረውን ሁሉን አቀፍ የለውጥ (ሪፎርም) ስራ የሚያጠናክር ነው ብለዋል።

ሰፊና ምቹ የስራ አካባቢ መፈጠሩ ለወንጀል ምርመራና መከላከል ስራዎች ቅልጥፍናን ይጨምራል ያሉት አዛዡ ተቋሙ ከተለመደው አሰራር ወጥቶ በቴክኖሎጂ የታገዘ የፖሊስ አገልግሎት ለመስጠት ለጀመረው ጥረት መሰረት ይሆናል ብለዋል።

የፖሊስ ተቋምን ወደ ላቀ ከፍታ የሚያሸጋግሩ ግዙፍ ግንባታዎችና ምቹ የስራ አካባቢን መፍጠር፣ ለላቀና ለተቀላጠፈ የህዝብ አገልግሎት ዋነኛ መሠረት መሆኑንም አረጋግጠዋል

በባህር ዳር፣ በደሴ እና በደብረ ብርሃን ከተሞች የሚከናወኑ እነዚህ ግንባታዎች የፖሊስን ክብርና ብቃት ከፍ የሚያደርጉ የከፍታ ዘመን ማሳያዎች መሆናቸውን ኮሚሽነሩ አጽንኦት ሰጥተዋል።

የተሻለ የስራ አካባቢ መፍጠር ማለት የተሻለ የህዝብ አገልግሎት መስጠት ማለት ነው ያሉት ኮሚሽነር ጀነራል ዘላለም መንግስቴ (ዶ/ር ) ፣ህንፃው ፖሊስ ግዳጁን በብቃት እንዲወጣ ትልቅ አቅም ይፈጥራል ብለዋል።

የግንባታው ሂደት በተቀመጠለት ጥራትና ፍጥነት ተጠናቆ ለታለመለት ዓላማ እንዲውልም አዛዡ አሳስበዋል።

የባህር ዳር ከተማ አስተዳደር ፖሊስ መምሪያ አዛዥ ኮማንደር ዋለልኝ ቢምረው በበኩላቸው፣ ግንባታው የክልሉ መንግስትና የህዝብ ድጋፍ የታከለበት መሆኑን ገልጸዋል።

ፖሊስ የህዝብ አገልጋይ እንደመሆኑ መጠን፣ ህብረተሰቡ ለሰላሙና ለደህንነቱ ሲባል ለተቋሙ እያደረገ ያለው ድጋፍ የሚደነቅ መሆኑን ጠቁመዋል።

ኮማንደሩ አክለውም፣ የከተማዋን ሰላምና ደህንነት በዘላቂነት ለመጠበቅ ወቅቱን የዋጀ አሰራር የግድ መሆኑንና ግንባታው ሲጠናቀቅ የከተማዋን ነዋሪዎች እርካታ በሚያረጋግጥ መልኩ አገልግሎት እንደሚሰጥ አረጋግጠዋል።

ይህ የቢሮ ግንባታ ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት ሲጀምር፣ የባህር ዳር ከተማ ፖሊስ መምሪያን የአገልግሎት አሰጣጥ ወደ አዲስ ምዕራፍ ያሸጋግረዋል ሲሉም ኮማንደር ዋለልኝ ቢምረው አክለዋል።

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Scroll to Top