“ኮሙኒኬሽን እና ህዝብ ግንኙነት ዋና መምሪያ ህዝብ እና ፖሊስን በማገናኘት ረገድ ያለበትን ሚና አጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል!” ኮሚሽነር ጀኔራል ዘላለም መንግስቴ (ዶ/ር)
የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና አዛዥ ኮሚሽነር ጀኔራል ዘላለም መንግስቴ (ዶ/ር) በዋና ጠቅላይ መምሪያው የኮሙኒኬሽንና ህዝብ ግንኙነት ዋና መምሪያ ያለውን የስራ እንቅስቃሴና ለሰራተኞች የተፈጠሩ ምቹ የስራ ሁኔታዎችን ተመልክተዋል።
ኮሚሽነር ጀኔራል ዘላለም መንግስቴ (ዶ/ር) በጉብኝታቸው ወቅት የፖሊስን ተልዕኮና የሰላም ግንባታ ሥራዎችን ለሕዝቡ ተደራሽ ለማድረግ የኮሙኒኬሽን ዘርፉ የሚጫወተው ሚና ከፍተኛ መሆኑን ገልጸዋል።
በዋና መምሪያው የሚገኘው የኮሙኒኬሽን መምሪያ የተቋሙን የዕለት ከዕለት ተግባራት ፈጣን፣ ግልፅና ቀልጣፋ በሆነ መንገድ ለህዝብ በማድረሱ ከሌሎች የመገናኛ ብዙኃን ጋር ተወዳዳሪና ተጽዕኖ ፈጣሪ እየሆነ መጥቷል ሲሉም ኮሚሽነሩ ተናግረዋል።
በዘርፉ የተሰማሩ ባለሙያዎች በቁርጠኝነትና በባለቤትነት ስሜት እያከናወኑት ያለውን ተግባርም አበረታተዋል።
ዘመኑን የዋጀ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን በመጠቀም የፖሊስን ገጽታ የመገንባትና የተሳሳቱ መረጃዎችን የመከላከል ሥራ ተጠናክሮ እንዲቀጥል አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል።
በሙዚቃና በውዝዋዜ፣ በማርች ባንድ እንዲሁም በስፖርት ተጨባጭ ውጤቶች የተመዘገቡ ሲሆን አሁን የተጀመረው የስራ አካባቢን የማስዋብና ራስን የማብቃት ስራ ተጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል ብለዋል።
ዘርፉን የበለጠ ውጤታማ ለማድረግ የሚያስፈልጉ የቁሳቁስ እና የሰው ኃይል የማሟላት ስራ ይሰራ ሲሉም ኮሚሽነር ጀኔራል ዘላለም መንግስቴ (ዶ/ር) ተናግረዋል።
ኮሚሽነር ጀኔራሉ በመምሪያው እየተከናወኑ ያሉ ተግባራትን የገመገሙ ሲሆን፣ በተለይም የፖሊስን ተልዕኮ ለህዝብ ተደራሽ ለማድረግ እየተሰሩ ያሉ ስራዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ አሳስበዋል።
እንደ ኮሚሽነር ጀኔራል ዘላለም መንግስቴ (ዶ/ር) ገለጻ ዋና መምሪያው ያደረገው የስራ አካባቢን የማስዋብና የመልሶ ጥገና ተግባር የተቋሙን የለውጥ ስራ የሚያጠናክር ነው።
ኮሚሽነር ጀኔራል ዘላለም መንግስቴ (ዶ/ር) የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን (አሚኮ) ለአማራ ክልል ፖሊስ ሚዲያ እያደረገ ላለው ዘርፈ ብዙ ድጋፍ ልዩ ምስጋና አቅርበዋል።
በቀጣይ የፖሊስን ገጽታ በመገንባትና ወቅታዊ መረጃዎችን ለህዝብ በፍጥነት በማድረስ ረገድ ሊሻሻሉ በሚገባቸው ጉዳዮች ላይ ኮሚሽነር ጀኔራል ዘላለም መንግስቴ (ዶ/ር) አቅጣጫ ሰጥተዋል።
የኮሙኒኬሽንና ህዝብ ግንኙነት ዋና መምሪያ ኃላፊ ረዳት ኮሚሽነር ክንዱ ወንዴ በበኩላቸው ኮሚሽነር ጀኔራሉና ማኔጅመንቱ ዋና መምሪያው ድረስ መጥተው የስራ እንቅስቃሴውን በመመልከታቸው ምስጋና አቅርበዋል።
ኮሚሽነር ጀነራል ዘላለም መንግስቴና ማኔጅመንቱ የስራ እንቅስቃሴያችንን መመልከታቸው ለስራችን ትልቅ መነቃቃት ይፈጥራል ብለዋል።
በጉብኝቱ ወቅት እንዲስተካከሉ የተሰጡ አቅጣጫዎችንም በቁርጠኝነት ለመፈጸም እንሰራለን ሲሉ ረዳት ኮሚሽነር ክንዱ ወንዴ አክለው ገልጸዋል።
በመጨረሻም የዋና መምሪያው የቴክኖሎጂ አጠቃቀሙን በማዘመንና የህዝብ ግንኙነት ስራውን በማጠናከር የክልሉን ሰላምና ጸጥታ ለማስከበር የሚደረገውን ጥረት ዜናና ፕሮግራሞችን መስራቱን እንደሚቀጥል ኃላፊው አስታውቀዋል።


















