በቴክኖሎጂ የታገዘ የወንጀል መከላከል ስራ መጀመሩን ፖሊስ ገለፀ።
የባህርዳር ከተማ አስተዳደር ፖሊስ መምሪያ በከተማዋ የሚፈፀሙ የወንጀል ድርጊቶችን ለመከላከልና ለመቆጣጠር በቴክኖሎጂ የታገዘ ስራ እየሰራ መሆኑን አስታውቋል።
የከተማ አስተዳደሩ ፖሊስ መምሪያ አዛዥ ኮማንደር ዋለልኝ ቢምረው እንደተናገሩት የባህርዳር ከተማን ሰላምና ደህንነት ለማረጋገጥ ዘመኑ የደረሰባቸውን ከስልሳ በላይ የደህንነት ካሜራዎች በመጠቀም የወንጀል መከላከል ስራ እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።
እንደ ኮማንደር ዋለልኝ ገለጻ ካሜራዎቹ የሰው ኃይል ድካምን እና ጊዜን ከመቆጠባቸው ባሻገር የፖሊስ አካላት በማይገኙበት ጊዜ ለሚፈፀሙ ወንጀሎች አጥፊዎችን ለመያዝ ከሚሰጡት ፋይዳ ባለፈ ለትራፊክ ቁጥጥር ስራም ከፍተኛ ሚና ይወጣሉ።
ይህ ዘመናዊ የፖሊስ አሰራር ዘዴ የክልሉ ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ የጀመረው የድጂታላይዜሽን ጉዞ አንዱ ማሳያ በመሆኑ በቀጣይም ሌሎች የቴክኖሎጂ ውጤቶችን ያካተተ የወንጀል መከላከል፣ የወንጀል ምርመራ እና የትራፊክ ቁጥጥር ስራ እንደሚሰራም አዛዡ አመላክተዋል።
አሰራርን ዘመናዊ እና ቀልጣፋ ከማድረግ አንጻርም በባህርዳር ከተማ አስተዳደር መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ውስጥ የባህርዳር ከተማ ፖሊስ ስራ መጀመሩንም ኮማንደሩ አስታውቀዋል።
በማዕከሉም ማንኛውም አካል የትኛውም ፖሊስ ጣቢያ መሄድ ሳይጠበቅበት ቅሬታ፣ ክስና ጥቆማ መስጠት የሚችል በመሆኑ ጊዜን፣ ድካምን እና እንግልትን መቀነስ ያስችላል ሲሉም ኮማንደር ዋለልኝ አክለው ገልፀዋል።
በቀጣይም ከትራፊክ ደንብና ቁጥጥር ጋር የተያያዙ የመቀጮና ሌሎች ጉዳዮችን ለመፍታት ፖሊስ ጣቢያ በመሄድ የሚፈጠረውን ድካምና እንግልት ለመቀነስ የሚያስችል አገልግሎት ለመጀመር መታሰቡንም አዛዡ ጠቁመዋል።
ረዳት ኢንስፔክተር ታደሰ ታየ በባህርዳር ከተማ አስተዳደር ፖሊስ መምሪያ የመሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት አሰጣጥ አቤቱታና ጥቆማ ባለሙያ በበኩላቸው ማህበረሰቡ ለሚኖረው ማንኛውም ጥቆማ፣ ክስ፣ አቤቱታ እና ቅሬታ የትም መሄድ ሳይጠበቅበት ጉዳዩን ማሳወቅ ይችላል ብለዋል።
አሰራሩ የባህርዳር ከተማ አስተዳደር ፖሊስ መምሪያን እና የከተማዋን ሁሉንም ፖሊስ ጣቢያዎች ጉዳይ ለመፍታት የሚያስችል እና የማህበረሰቡን ድካም መቀነስ የሚያስችል ስለመሆኑም ረዳት ኢንስፔክተሩ ተናግረዋል።











