የህገ-ወጥ ታጣቂ ቡድኑ አመራር እና አባላት በሰላማዊ መንገድ እጅ ሰጥተዋል፡፡
በደራ፣ በወጊዲ፣ በሸበል በረንታ በአባይ ዳር መገናኛዎች ዙሪያ ባለፈው ሳምንት በተካሄደ የተቀናጀ ኦፕሬሽን ተበታትኖ የነበረው ራሱን በተለያዬ ስያሜ የሚጠራው የታጣቂ ቡድኑ አመራርና አባላት በሰላም እጅ ሰጥተዋል፡፡
በዕለቱ የ6ኛ ዕዝ አዛዥ ሜጀር ጀኔራል ብርሃኑ ጥላሁንን ጨምሮ የወረዳው የስራ ሃላፊዎች፣ የሠራዊቱ ከፍተኛ አመራሮች የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎችና የአካባቢው ማህበረሰብ በመገኘት አቀባበል አድርገውላቸዋል።
ሜጀር ጀኔራል ብርሃኑ ጥላሁን ምንጊዜም ቢሆን ኢትዮጵያዊነትን በማስቀደምና በምክክርና በውይይት የትኛውንም ችግር መፍታት እንደሚቻል በማመን መሳሳታችሁን ተረድታችሁ የሰላም ጥሪውን ተቀብላችሁ በመምጣታችሁ ምስጋና ይገባችኋል ብለዋል።
ዋና አዛዡ ፍላጎትን በኃይል ለማሳካት መሞከር ትርፋ ኪሳራ ብቻ ሲሆን የኋላ ቀር አስተሳሰብ ያላቸው ቆሞ ቀሮች የሚከተሉት የጥፋት መንገድ እንደሆነም አስረድተዋል።
እንደ ሜጀር ጀኔራል ብርሃኑ ገለጻ ኢትዮጵያ በአሁኑ ሰዓት ታላላቅ የልማት ስራዎችንና ሌሎች ሀገራዊ ጉዳዮችን ለማሳካት ጥረት እያደረገች ባለችበት ወቅት እንቅፋት መፍጠር የታሪክ ተወቃሽ ያደርጋል።
አሁንም በጫካ የሚገኙ ታጣቂ ቡድኖች ያለምንም ማመንታት ፈጥነው የሰላም ጥሪውን ተቀብለው መግባት እንዳለባቸውም ሜጀር ጀኔራል ብርሃኑ ጥላሁን ጥሪ አቅርበዋል።
የደራ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ መስፍን ታዬ በበኩላቸው የወረዳችን ሰላም በህገወጥ ታጣቂ ኃይሎች ላለፉት አመታት ብዙ በደል እየፈፀሙ እንደመጡ አስታውሰው በሰላም ወዳዱ ህዝባችን እና በመከላከያ ሰራዊታችን ብርቱ ክንድ ውጥናቸው ሊመክን ችሏል ብለዋል፡፡
በደራ ወረዳ ቀጠና ታጥቆ ሲንቀሳቀስ የነበረው ህገወጥ ታጣቂ ቡድኑ ራሱን የሚኒሊክ ዕዝ የበላይ ፍቃዱ ክፍለ ጦር ብሎ የሚጠራው ዋና አሰተባባሪ በየነ ግዛው ትግሉ ከመነሻ ይህ ነው የሚባል አላማ የሌለው መሆኑን ገልጾ ለሶስት አመታት የህዝብን ስቃይ ከማብዛት ውጭ የምናስገኝለት አንድም ጥቅም እንደሌለ ተረድተን የሰላም ጥሪውን ተቀላቅለናል ብሏል።
ፅንፈኛ ቡድኑ አሁን ላይም በህዝብ ላይ ያደረሰው እንግልትና ስቃይ አልበቃ ብሎት ይባስ ትግሉ ቀስበቀስ ተጠልፎ ከኢትዮጵያ ጠላቶች ጋር ግንባር ፈጥሮ መስራቱን ስናውቅ ከባዳ ጋር በመሆን ህዝባችንን አንወጋም በማለት ከህዝባችን ጎን ለመሆን ተመልሰናል ብሏል።
ሌላኛው አቶ በቀለ አበጀ ከሶስት አመታት በፊት በደራ ወረዳ ውስጥ ባይት ቀበሌ ሚሊሺያ ሆኖ ሲያገለግል የነበረው በኋላም በፅንፈኛ ቡድኑ ፕሮፓጋንዳ ተታሎ የተሰጠውን የህዝብና የመንግስት ሃላፊነት ወደ ጎን ትቶ አስከ አሁን በህዝብ ላይ ባደረሰው የክህደት ተግባር በመፀፀት 64 ግብረ አበሮችን ጭምር አስተባብሮ ከነ ሙሉ ትጥቃቸው ይዞ እንደገባ ተናግሯል።





