“ሰላማችን በህዝባችን ደህንነት ላይ የተመሰረተ ነው” የ38ኛ ሻለቃ የአድማ መከላከል ፖሊስ አባላት።
የአንድ ሀገር ሉዓላዊነት መከበርና በኢኮኖሚ ራስን የመቻል ጉዞ ዋነኛ መሰረቱ የዜጎች ሰላምና ደህንነት መረጋገጥ መሆኑ ይታመናል።
ይህንን ታላቅ አገራዊ ግብ ለማሳካት ደግሞ የሀገሪቱ የጸጥታ ኃይል ግንባር ቀደም የጀርባ አጥንት በመሆን የአንበሳውን ድርሻ ይወጣል።
ኢትዮጵያ ከጥንት እስከ ዛሬ በውጭ ባዕዳንና በውስጥ ባንዳዎች የተቃጡባትን ተግዳሮቶች በጀግኖች ልጆቿ ተጋድሎ እየመከተች፣ ሉዓላዊነቷን ሳታስደፍር የነፃነት ቀንዲል ሆና ገድሏን በወርቅ ብዕር መዝግባ ቆይታለች።
በአሁኑ ወቅትም በአማራ ክልል የተፈጠረውን ግጭት ተከትሎ የመጣውን ማህበረሰባዊ ኪሳራ ለመቀልበስና አስተማማኝ ሰላም ለማስፈን የህግ ማስከበር ስራው ተጠናክሮ ቀጥሏል።
መነሻውን ከህዝብ መድረሻውን ደግሞ ኢትዮጵያ ያደረገው የአማራ ክልል አድማ መከላከል ፖሊስ፣ የሀገርን ህልውና ለማረጋገጥ በአንዲት ህይወቱን በማስያዝ የማይደበዝዝ ገድል እየፈጸመ ይገኛል።
የክልሉን ሰላም ከሚያረጋግጡ የቁርጥ ቀን ልጆች መካከል 38ኛ ሻለቃ የአድማ መከላከል ፖሊስ አባላት፣ በችግሮች ተፈትኖ የተወለደ የሚፈጠሩ ችግሮችን ጀግንነትና በተግባር እያሳየ ይገኛል።
የሻለቃው የሰው ሀይል አስተዳደርና ሎጀስቲክስ ኃላፊ ዋና ኢንስፔክተር አዲሱ አዳነ እንደተናገሩት፣ የህዝብን ሰላም መጠበቅ ቀዳሚ ኃላፊነታቸው ነው።
የህዝባችን ሰላም እስኪረጋገጥ ድረስ የምንከፍለው ሁሉን አቀፍ መስዋዕትነት ያኮራል እንጂ ከዓላማችን አይገታንም ሲሉ የጸና አቋማቸውን ገልጸዋል።
ዋና ኢንስፔክተሩ አክለውም፣ ከታሪካዊ ጠላቶች ጋር ተባብሮ የህዝብን ስቃይ ማራዘም ከክህደትም በላይ ባንዳነት መሆኑን ጠቁመው፤ ወቅቱ ሰላምን ብቸኛ ምርጫ በማድረግ ለህዝብ ሰላም መታገል የሚጠይቅ የትውልድ ግዴታ ያለበት ጊዜ መሆኑን አመላክተዋል።
የሻለቃው አባላት በበኩላቸው፣ የማህበረሰቡን ሰላም የሚነሱ አካላትን እኩይ ተግባር በማክሸፍ የልማት ተጠቃሚ ማህበረሰብ እስኪፈጠር ትግላቸው እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።
እረፍትና እርካታችን በህዝባችን ሰላም ላይ የተመሰረተ ነው ያሉት አባላቱ በተሳሳተ መንገድ ታጥቀው ሰላም የሚነሱ አካላት የቀረበላቸውን የሰላም አማራጭ ተቀብለው የጋራ ጠላትን በጋራ ለመመከት እንዲሰለፉ ጥሪ አቅርበዋል።
ህዝቡ በሰላም ወጥቶ እንዲገባ፣ አርሶ አደሩ እንዲያመርትና ነጋዴው ነግዶ እንዲያተርፍ የሚያስፈልገውን የሰላም አየር ለማረጋገጥ በቁርጠኝነት እየሰሩ እንደሚገኙም ጠቁመዋል።
በአሁኑ ወቅት ሻለቃው በክልሉ በተለያዩ አካባቢዎች ተሰማርቶ የህግ ማስከበር ስራውን በላቀ ዝግጅትና በህዝባዊ ወገንተኝነት እያከናወነ ይገኛል።









