በደቡብ ጎንደር ዞን የተቃጣው የጥፋትና የዝርፊያ ሙከራ በጸጥታ ኃይሉ የተቀናጀ እርምጃ መከሸፉ ተገለጸ።
በዛሬው ዕለት በደቡብ ጎንደር ዞን በፎገራ ወረዳና በወረታ ከተማ የጥፋት ተልዕኮ አንግቦ የተንቀሳቀሰው የህገ-ወጥ ታጣቂው ቡድን፣ በጸጥታ ኃይሉ በተሰነዘረበት የተቀናጀ እርምጃ ከፍተኛ ሰብአዊና ቁሳዊ ኪሳራ ደርሶበታል።
እንደ አማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያው ገለጻ የጥፋት ቡድኑ በዛሬው ዕለት በወረታ ከተማ እና በፎገራ ወረዳ የህዝብን ሰላም ለማናጋትና የንብረት ዘረፋ ለመፈጸም ሙከራ ቢያደርግም የጸጥታ ኃይሉ ከህዝቡ ባገኘው ጥቆማና ባደረገው ስትራቴጂካዊ ኦፕሬሽን የህገ ወጥ ቡድኑ ሙት እና ቁስለኛ እንደሆነም አረጋግጧል።
ህገ-ወጥ ቡድኑ በደረሰበት ከፍተኛ ምት የተነሳ መቋቋም አቅቶት ሙትና ቁስለኛ የሆኑ የቡድን አጋሮቹን እያንጠባጠበ ወደ መጣበት መፍርጠጡን ዋና ጠቅላይ መምሪያ አረጋግጧል።
ይህ የተቀናጀ የመከላከል እርምጃ የቡድኑን የጥፋት አቅም ያዳከመ ሲሆን፣ የጸጥታ ኃይሉ ቀሪውን የቡድን አባል ሙሉ በሙሉ ለመደምሰስ በቁርጠኝነት እየተንቀሳቀሰ እንደሚገኝም ጠቅላይ መምሪያው ገልጿል።
የክልሉ ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ እንዳለው፣ ይህ ህገ-ወጥ ቡድን የሀገር ግንባታ ሳይሆን የሀገር ማፍረስ ተልዕኮ አንግቦ የሚንቀሳቀስ ነው።
ቡድኑ ኢትዮጵያን ለማዳከም ካሰፈሰፉ የውጭና የውስጥ ጠላቶች የተሰጠውን የጥፋት አጀንዳ ለማስፈጸም እንደሚሰራ የጠቀሰው መምሪያው፣ ዋና ግቡም የዜጎችን እና የመንግስትን ሀብት በመዝረፍ የግል ጥቅሙን ማሳደግ እንደሆነ አጋልጧል።
ቡድኑ ለህዝብ ደህንነትና ለሀገር ሉዓላዊነት ደንታ የሌለው መሆኑም አመላክቷል።
ማንኛውንም የጥፋት ሙከራ በፅናት ለመከላከል የጸጥታ ኃይሉ በሙሉ ዝግጁነትና በተጠንቀቅ እንደሚገኝ ገልጾ ከፌዴራል የጸጥታ ግብረ-ኃይል ጋር በከፍተኛ መናበብና ቅንጅት እየሰራ እንደሚገኝም ጠቁሟል ።
የክልሉን ሰላምና የዜጎችን ደህንነት አሳልፎ ለሚሰጥ ማንኛውም የጥፋት ኃይል የማይበገር ክንድ እንዳለውና ማንኛውንም መስዋዕትነት ለመክፈል ከፍተኛ ዝግጅት ማድረጉን በድጋሚ አረጋግጧል።
ይህን የጥፋት ቡድን ሙሉ በሙሉ ለማጥፋትና ቀጣይነት ያለው ሰላም ለማረጋገጥ ህብረተሰቡ እንደ ትላንቱ ከጸጥታ ኃይሉ ጎን በጽናት እንዲቆምና አጠራጣሪ እንቅስቃሴዎችን እንዲጠቁም ጠይቋል።
ለተገኘው ድል ህብረተሰቡ ከጸጥታ ኃይሉ ጎን በመሰለፍ ላሳየው ትብብር እና የጸጥታ ኃይሉ አባላት ላሳዩት የተቀናጀ አፈፃፀም የክልሉ ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ ከፍተኛ አድናቆቱን ለግሷል።
የክልሉ የጸጥታ ኃይል ለሕዝቡ ሰላምና ደህንነት ቁርጠኛ መሆኑንና ማንኛውንም የሕግ ጥሰት በቆራጥነት እንደሚታገል ዋና ጠቅላይ መምሪያው አጽንኦት ሰጥቶታል።

