በእንጅባራ ከተማ 105 በርሚል ህገ-ወጥ ነዳጅ የጫነ ተሽከርካሪ በቁጥጥር ስር ዋለ
በአዊ ብሄረሰብ አስተዳደር ዞን እንጅባራ ከተማ፣ ጥር 28 ቀን 2018 ዓ.ም. 105 በርሚል ህገ-ወጥ ነዳጅ በመጫን ወደ ቻግኒ ከተማ ሊወጣ የነበረ ተሽከርካሪ በጸጥታ ኃይሎች መያዙ ተገለጸ።
የሰሌዳ ቁጥሩ (ኮድ 3) A33038 ET የሆነው የ’ካሶኒ’ ተሽከርካሪ ነዳጁን ጭኖ ከከተማዋ ለመውጣት ሲሞክር በቻግኒ መውጫ ኬላ ላይ በጸጥታ ኃይሎች ክትትል በቁጥጥር ስር ሊውል ችሏል።
የእንጅባራ ከተማ ፖሊስ ጣቢያ ወንጀል መርማሪ ዋና ሳጅን ታከለ ብርሃን እንደገለጹት፤ ግለሰቡ ህገ-ወጥ ድርጊቱን ሲፈጽም እጅ ከፍንጅ ተይዟል።
ፖሊስ በአሽከርካሪው አቶ ዳውድ ሰይድ ላይ አስፈላጊውን ምርመራ በፍጥነት አጣርቶ ለፍትህ አካላት መላኩን አስታውቋል።
ዓቃቤ ህግ ምስክሮችን በማሰማት ሂደቱን የቀጠለ ሲሆን የአዊ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤትም ተከሳሹን ለብይን ለየካቲት 9 ቀን 2018 ዓ.ም. ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።
በተጨማሪም በፍርድ ቤቱ ውሳኔ መሰረት የተያዘው 105 በርሚል ነዳጅ በሞዴል 85 ተሸጦ ገቢው እንዲቀመጥ ተወስኗል።
አሁን ላይ ተከሳሹ በህግ ጥላ ስር ሆኖ የፍርድ ሂደቱን እየተከታተለ ይገኛል።
ይህ እርምጃ በህገ-ወጥ የነዳጅ ዝውውር ላይ የሚደረገውን ቁጥጥር አጠናክሮ ለመቀጠል ካለው እቅድ አንዱ አካል መሆኑ ተጠቁሟል።




