በቡሬ ከተማ የማህበረሰብ አቀፍ ሰላምን የማረጋገጥ ንቅናቄ ተካሄደ
በምዕራብ ጎጃም ዞን በቡሬ ከተማ አስተዳደር ቀበሌ 04 “በጀግንነት መጠበቅ በሰብዓዊነት ማገልገል” በሚል መሪ ቃል የማህበረሰብ አቀፍ የወንጀል መከላከል የሰላም ቀን በድምቀት ተከበረ።
መድረኩ የፀጥታ አካላትና ህብረተሰቡ በጋራ በመቆም የአካባቢያቸውን ሰላም በዘላቂነት ለማረጋገጥ ያላቸውን ቁርጠኝነት የታየበት ሆኗል።
በዕለቱ የቀበሌ 04 ፖሊስ ኦፊሰር ዋና ሳጅን አባይነህ ሙሉ ባቀረቡት ሪፖርት፣ በአካባቢው የፖሊስ አደረጃጀቶችን በንቃት በመጠቀማቸው ቀደም ሲል ይከሰቱ የነበሩ ወንጀሎች በከፍተኛ ሁኔታ መቀነሳቸውን፤ምንም አይነት የነፍስ ግድያ ወንጀል አለመመዝገቡን እና ግጭቶችን በአካባቢው የሰላም ኮሚቴዎች አማካኝነት በውይይት መፍታት መቻሉን ገልጸዋል።
የቡሬ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አቶ ሀይማኖት አሰፋ እና የዞኑ ፖሊስ መምሪያ ኃላፊ ኮማንደር ተሾመ ብዙ ባስተላለፉት መልዕክት፣ ሰላም ለማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እድገት መሰረት መሆኑን ጠቅሰው፤ ህብረተሰቡ አደረጃጀቶቹን በመጠቀም የወንጀል ስጋቶችን ቀድሞ የመከላከል ስራውን አጠናክሮ እንዲቀጥል አሳስበዋል።
የከተማው ፖሊስ ጽ/ቤት ኃላፊ ኮማንደር አዱኛው አየነው በበኩላቸው፣ ቡሬ ቀደም ሲል ከነበረባት የወንጀል ስጋት ወጥታ አሁን ላይ ነዋሪው ያለ ስጋት የልማት ስራውን እያከናወነ መሆኑን ገልፀዋል።
የአካባቢው ነዋሪዎች በሰጡት አስተያየት፣ በምሽት ሮንድ በመጠበቅና ሰርጎ ገቦችን በመከታተል የከተማዋን ሰላም ታድገው እንደሚቀጥሉ ቃል ገብተዋል።
በፕሮግራሙ ማጠቃለያም ለሰላም መጠበቅ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ላበረከቱ ተቋማት፣ የሚሊሻ አባላትና ግለሰቦች የሰላም አምባሳደርነት የክብር ምስክር ወረቀት ተበርክቶላቸዋል።





