በሰሃላ ወረዳ በባጃጅ ተጭኖ ሲጓዝ የነበረ ከ4 ሺህ በላይ የጦር መሳሪያ ጥይት በቁጥጥር ስር ዋለ

በሰሃላ ወረዳ በባጃጅ ተጭኖ ሲጓዝ የነበረ ከ4 ሺህ በላይ የጦር መሳሪያ ጥይት በቁጥጥር ስር ዋለ

በዋግኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን በሰሃላ ወረዳ ፖሊስ በተደረገ ድንገተኛ ፍተሻ በባጃጅ ተጭኖ ወደ መሸሃ ከተማ ሊገባ የነበረ ከፍተኛ ቁጥር ያለው የብሬንና የክላሽንኮቭ ጥይት መያዙን ኢንስፔክተር ጌታወይ አብርሃ የሰሃላ ወረዳ ፖሊስ ጽሕፈት ቤት አዛዥ አስታውቀዋል።

የፖሊስ መረጃ እንደሚያመለክተው የሰሌዳ ቁጥሩ ኮድ-1 አማ 73849 የሆነ ባጃጅ ከፅሓየ ካምፕ ተነስቶ ወደ 01 ቀበሌ መሸሃ ከተማ በማቅናት ላይ እያለ ነው በወረዳው ፖሊስ ፍተሻ የተደረገበት።

በፍተሻውም 880 የብሬን ጥይቶች እና 4,000 የክላሽ ጥይቶች በድብቅ ተጭነው ተገኝተዋል ሲሉ ነው ኢንስፔክተር ጌታወይ።

ከድርጊቱ ጋር በቀጥታ ግንኙነት አላቸው የተባሉ ሁለት ግለሰቦች ከነጥይቶቹ ጋር በቁጥጥር ስር ውለዋል።

ፖሊስ በአሁኑ ወቅት በቁጥጥር ስር በሚገኙት ተጠርጣሪዎች ላይ ጥልቅ ምርመራ እያካሄደ መሆኑን የገለጸ ሲሆን፣ ተተኳሾቹ የት ለመድረስ እንደታሰቡና ተያያዥ መረጃዎችን የማጣራት ስራ እየተሰራ መሆኑንም የሰሃላ ወረዳ ፖሊስ ጽሕፈት ቤት አዛዥ አክለው አስታውቀዋል።

ህገ-ወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውርን ለመግታት ህብረተሰቡ እያደረገ ያለውን ጥቆማና ትብብር አጠናክሮ እንዲቀጥል ፖሊስ ጥሪውን አስተላልፏል።

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Scroll to Top