ተሰርቀው የተቀመጡ የተለያዩ የኤሌክትሪክ ማስተላለፊያ ሽቦዎችን መያዙን ፖሊስ ገለፀ።
ንብረትነታቸው የተለያዩ ፋብሪካዎች እና ድርጅቶች የሆኑ በርካታ ልዩ ልዩ የኤሌክትሪክ ማስተላለፊያ ገመዶች፣የግንባታ ፌሮ ብረቶች እና መሰል ሽቦዎች ከተከማቹበት ቦታ በቁጥጥር ስር ማዋሉን የባህርዳር ከተማ አስተዳደር ፖሊስ መምሪያ አስታውቋል።
በከተማ አስተዳደሩ ፖሊስ መምሪያ የኢኮኖሚና ልዩ ልዩ ወንጀሎች ምርመራ ክፍል ኃላፊ ምክትል ኢንስፔክተር ፈለቀ ታሪኩ እንደተናገሩት እነዚህ የመሰረተ ልማት አካል የሆኑ የኤሌክትሪክ ገመዶች በባህርዳር ከተማ አስተዳደር አፄ ቴዎድሮስ ክፍለ ከተማ ምድረ ገነት ቀበሌ ከማህበረሰቡ በተሰጠ ጥቆማ እና በተደረገ ፍተሻ ከአንድ ያገለገሉ ዕቃዎች መሸጫ በተለምዶ (ቆራሊዮ) መደብር ውስጥ መያዛቸውን ተናግረዋል።
ከጉዳዩ ጋር በተያያዘም ሁለት ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ እየተጣራ ሲሆን ሌሎች ተጠርጣሪዎችን ለመያዝም ክትትል እየተደረገ እንደሚገኝ ኃላፊው አስታውቋል።
በተመሳሳይ በአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን በመሠረተ ልማት አውታሮች ላይ የዘረፋ ወንጀል የፈፀሙ ተጠርጣሪዎች በህግ ቁጥጥር ስር ውለው ፖሊስ አስፈላጊውን ምርመራ እያጣራ መሆኑን የዞኑ ፖሊስ መምሪያ አሰታውቋል።








