ለከተማዋ ሰላም መረጋገጥ በቁርጠኝነት የሚተጋ የፖሊስ ኃይል ተፈጥሯል።
ባለፉት ስድስት ወራት ማህበረሰቡን ያሳተፈ የጸጥታ ስራን በመስራቱ የወንጀል መከላከልና የምርመራ ስራዎችን ውጤታማ በሆነ መንገድ ማከናወኑን የዳንግላ ከተማ ፖሊስ ጽሕፈት ቤት ገለጿል ።
የዳንግላ ከተማን ጸጥታና ደህንነት በዘላቂነት ለማረጋገጥ፣ ሌት ተቀን የሚተጋና ዝግጁነቱ የተሟላ የፖሊስ ኃይል መገንባቱን በአዊ ብሄረሰብ አስተዳደር ፖሊስ መምሪያ የዳንግላ ከተማ ፖሊስ ፅህፈት ቤት አዛዥ ዋና ኢንስፔክተር ጀጃው ሞላ ገልጸዋል።
የጽሕፈት ቤቱ አዛዥ ዋና ኢንስፔክተር ጀጃው ሞላ እንደገለጹት፤ የከተማዋ ፖሊስ ሰራዊት ከመደበኛው የወንጀል መከላከል ተግባር ባለፈ፣ የከተማዋን ሰላም አስተማማኝ ለማድረግ በልዩ ትኩረት እየሰራ ይገኛል ብለዋል።
ሰርጎ ገብነትን፣ ሕገ-ወጥነትንና የሕዝብን ሰላም የሚያውኩ ድርጊቶችን ለመግታት የኬላ ፍተሻና የትራፊክ ቁጥጥር ስራዎች በከፍተኛ ንቃት እየተከናወኑ መሆኑንም አዛዡ ጠቁመዋል።
ባለፉት ስድስት ወራት በተከናወኑ የወንጀል ምርመራ ስራዎች ውጤታማ ተግባራት መከናወናቸውን አዛዡ አክለዋል ።
ፖሊስ የሕዝብ አገልጋይ በመሆኑ ማኅበረሰቡ ለጸጥታ ኃይሉ ዓይንና ጆሮ በመሆን በወንጀል መከላከል ተግባር ላይ ቀጥተኛ ተሳትፎ ሊያደርግ ይገባል ሲሉ ዋና ኢንስፔክተር ጀጃው ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።
በጽሕፈት ቤቱ የማኅበረሰብ አቀፍ ወንጀል መከላከል ንዑስ ክፍል ኃላፊ ዋና ሳጅን ማሩ ፈንታሁን፤ ከወቅታዊ የጸጥታ ሁኔታ ጋር ተያይዞ ተቀዛቅዞ የቆየውን የማኅበረሰብ አቀፍ ፖሊስ አገልግሎት በላቀ ደረጃ ለመጀመር ዝግጅት መጠናቀቁን ገልጸዋል።
ይህ አሰራር ለከተማዋ ሰላምና ልማት ወሳኝ መፍትሔ መሆኑንም አክለው ገልጸዋል።






