የአማራ ክልል ፖሊስ የላቀ የሥራ አፈጻጸም ላሳዩ መኮንኖችና አባላት የማዕረግ እድገትና የአገልግሎት ሜዳይ ሽልማት ሰጠ
በዛሬው ዕለት በተካሄደ ስነ-ስርዓት በአገልግሎት ዘመናቸው ከፍተኛ የኃላፊነት ስሜትና ጀግንነት ላሳዩ ከፍተኛ መኮንኖች የማዕረግ እድገት የሰጠ ሲሆን፣ ከአስር ዓመት በላይ በቆራጥነት ላገለገሉ የሰራዊቱ አባላትም የሜዳይና የዕውቅና ሽልማት ተበርክቷል።
የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ ምክትል ኮሚሽነር እና የወንጀል ምርመራ ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ምክትል ኮሚሽነር ታደሰ አያሌው በመርሃ-ግብሩ ላይ ባደረጉት ንግግር የማዕረግ እድገቱ እና የአገልግሎት ሽልማቱ የሰራዊቱን ሞራል ለመገንባትና የሕዝብን ሰላም በዘላቂነት ለማስከበር የሚደረገው ጥረት አካል መሆኑን ገልጸዋል።
የአማራ ክልል ፖሊስ ሰራዊት በታሪክ አጋጣሚዎች ሁሉ የክልሉንና የሀገሪቱን ሰላም ለማስጠበቅ ወደር የሌለው መስዋዕትነት መክፈሉንም ያስታወቁት ምክትል ኮሚሽነር ታደሰ ይህ የማዕረግ እድገት እና የሜዳይ ሽልማት በፈተናዎች ውስጥ ፀንታችሁ ለቆማችሁና ለክልሉ ሕዝብ ጋሻ ለሆናችሁ ጀግኖች የሚገባ እውቅና ነው። ይህ ማዕረግ ከክብር በላይ ታላቅ የሕዝብ አደራ ነው! ሲሉም አክለው አብራርተዋል።
ዛሬ የምንሰጠው ይህ የማዕረግ እድገትና የሜዳይ ሽልማት ተራ ስጦታ አይደለም፤ መስዋዕትነት የተከፈለበት፣ ለክልሉ ሰላም እና ለሕዝብ ደኅንነት ሲባል ለታየ ፅናት የተሰጠ ክብር ነው ያሉት ደግሞ ረዳት ኮሚሽነር አያልነህ ተስፋዬ ምክትል ኮሚሽነር እና የአስተዳደርና ልማት ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ናቸው።
በፈተናዎች ውስጥ ፀንታችሁ ክልሉን ከመፍረስ የታደጋችሁ ጀግኖች በመሆናችሁ ኩራት ይሰማናል ያሉት ረዳት ኮሚሽነር አያልነህ የማዕረግ እድገቱ እና የአገልግሎት ሜዳይ ሽልማቱ ተጨማሪ ኃላፊነትንና ለሕዝብ ይበልጥ ማገልገልን የሚያመለክት መሆኑን አሳስበዋል።
ፖሊስ ሰራዊታችን በቆራጥነትና በታማኝነት የሕዝብ ጋሻ መሆኑን አረጋግጧል። መንግስትም የሰራዊቱን አቅም ለመገንባትና ጥቅማ ጥቅሙን ለማስከበር ትኩረት ሰጥቶ ይሰራል፤ እናንተም የተሰጣችሁን አደራ በላቀ ዲሲፕሊን እንድትወጡ አሳስባለሁ ሲሉ ረዳት ኮሚሽነር አያልነህ ተስፋዬ ምክትል ኮሚሽነር እና የአስተዳደርና ልማት ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ በአጽንኦት አብራርተዋል።
ረዳት ኮሚሽነር አብዮት ሽፈራው የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ የሰው ኃብት አስተዳደርና ልማት ዋና መምሪያ ኃላፊ በበኩላቸው ይህ ዛሬ የተሰጣችሁ ማዕረግና ሜዳይ የሰራዊታችን የትግል ወኔ የሚያድስ ነው ብለዋል።
በተለይ ባለፉት ጥቂት ዓመታት በክልላችን ላይ የተጋረጡ የፀጥታ ስጋቶችን በጀግንነት መክታችሁ ለዛሬው ሰላም መገኘት መሰረት ለሆናችሁ የፖሊስ ሰራዊቶች ምስጋናችን የላቀ ነው። ይህ እድገት ግን የክብር ብቻ ሳይሆን፣ ወደፊት የሚጠብቁንን ፈተናዎች በብቃት እንድንወጣ የሚያስገድድ የአደራ ምልክትም ጭምር ነው ሲሉ ረዳት ኮሚሽነር አብዮት ሽፈራው አክለው ገልጸዋል።
ባለፉት ዓመታት በተለያዩ የስራ ክፍሎች ሰላም ማስከበር እና የሕዝብን ደኅንነት በማስጠበቅ ስራዎች ላይ ተሰማርተው በማገልገላቸው ‘የላቀ አገልግሎት ሜዳይ’ እና ‘የማዕረግ እድገት’ ተሸላሚ የሆኑ የፖሊስ ሰራዊቶች እንደገለጹት የተሰጠን ማዕረግ እና ሜዳይ በቀሪው የአገልግሎት ዘመናችን በበለጠ ወኔ እንድሰራ ያበረታታናል ብለዋል።
ይህ ሽልማት በትከሻችን ላይ ያለውን ኃላፊነት ይበልጥ ያከብደዋል። ለበርካታ ዓመታት በቆራጥነት ያገለገልነው ለወገንና ለሀገር ብለን ነው። ዛሬ ድካማችን ታይቶ የማዕረግ እድገት እና የጀግንነት ሜዳይ ሲሰጠን፣ ነገም ለክልላችን ሰላም ደማችንን ለመገበርና ሕዝባችንን ከጥቃት ለመከላከል አዲስ ቃል የምንገባበት አጋጣሚ ሆኖልናል ሲሉ አክለዋል።
በዕለቱ የተሰጠው የማዕረግ እድገት የክልሉን የፖሊስ ሰራዊት የአመራር ሰንሰለት ይበልጥ እንደሚያጠናክርና በሁሉም አካባቢዎች አስተማማኝ ሰላም እንዲሰፍን ለሚደረገው ጥረት ትልቅ ግብዓት እንደሚሆን ተመልክቷል።
ከሐምሌ 1/2017 ዓ.ም እስከ ታህሳስ 30/2018 ዓ.ም ድረስ ወንድ= 2784 ሴት= 207 በድምሩ= 2991 የፖሊስ ሰራዊቶች ከረዳት ሳጅን እስከ ኮማንደር ማዕረግ እድገት የተሰጣቸው መሆኑን እንዲሁም ወንድ= 400 ሴት= 8 በድምሩ= 408 የፖሊስ የሰራዊቶች ደግሞ የአገልግሎት ሜዳይ ሽልማት ማግኘታቸውን ከዋና ጠቅላይ መምሪያው የሰው ኃብት አስተዳደርና ልማት ዋና መምሪያ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።












