የንቃትና የቁርጠኝነት ውጤት ፣ በጋዝጊብላ ወረዳ የጥፋት መልዕክተኞች ሴራ በፖሊስ ብልሃት ከሸፈ
በዋግ ኽምራ ዞን፣ በጋዝጊብላ ወረዳ ልዩ ስሙ አስከተማ ተብሎ በሚጠራው ወደ ላሊበላ መውጫ ኬላ ላይ፣ የፖሊስ ሰራዊት ባሳየው ከፍተኛ የጸጥታ ንቃትና ብልሃት ለጥፋት ኃይሎች ሊተላለፍ የነበረ ከፍተኛ የጦር መሣሪያ ጥይት በቁጥጥር ስር ማዋሉን የጋዝጊብላ ወረዳ ፓሊስ ጽ/ቤት አስታውቋል።
መነሻውን ከትግራይ ክልል ማይጨውና ኮረም በማድረግ ወደ ላሊበላ ሲጓዝ የነበረው ሰሌዳ ቁጥሩ 3-አ.አ 88593 የሆነ አይሱዙ ተሽከርካሪ፣ የጥፋት መሣሪያውን ለመደበቅ 47.5 ኩንታል የእንስሳት መኖ እንደ ሽፋን ተጠቅሞ ነበር ሲሉ ኢንስፔክተር ግርማ እሸቴ የጋዝጊብላ ወረዳ ፓሊስ ጽ/ቤት አዛዥ ጠቁመዋል።
ሆኖም ግን ይላሉ አዛዡ “በጀግንነት መጠበቅ፣ በሰብአዊነት ማገልገል” የሚለውን መመሪያ አንግቦ ሌት ተቀን የሚተጋው የጋዝጊብላ ወረዳ ፖሊስ፣ በተሽከርካሪው ላይ ባደረገው ጥብቅ ፍተሻ የሽፋን መኖውን ውስጡን በመፈተሽ ከሥሩ ተቀብሮ የነበረውን ተተኳሽ ጥይት ማጋለጥ ተችሏሉ ብለዋል።
በፍተሻው ወቅት በአጠቃላይ 47 ሳጥን የጦር መሣሪያ ተተኳሾች ተገኝተዋል ያሉት አዛዡ ዝርዝራቸውም
የብሬን ጥይት፡ 4,500 (9 ሳጥን)
የድሽቃ ጥይት፡ 6,349 (37 ሳጥን)
የክላሽ ጥይት፡ 75
ጠቅላላ ድምር፡ 10,924 ተተኳሽ ጥይት በቁጥጥር ስር መዋሉን አረጋግጠዋል።
በተጨማሪም ይሄው የጥፋት ቡድን ከዚህ ቀደም ሲጠቀምባቸው የነበሩና መረጃዎችን ሲያስተላልፍባቸው የነበሩ ማስታወሻዎች አብረው መያዛቸውንም አጠናክረዋል።
ምንም እንኳ አሽከርካሪው ለጊዜው መኪናውን ትቶ ከአካባቢው ቢሰወርም፣ ፖሊስ ግለሰቡን በቁጥጥር ስር ለማዋል ጥብቅ ክትትል እያደረገ እንደሚገኝም አዛዡ አስታውቀዋል።
ይህ ስኬታማ ኦፕሬሽን የተከናወነው በፖሊስ ብቻ ሳይሆን፣ የአካባቢው ነዋሪዎች፣ ወጣቶች፣ የመከላከያ ሰራዊት አመራሮች፣ የዞኑና የወረዳው የጸጥታ መዋቅሮች በጋራ ባደረጉት የተቀናጀ ጥረት እንደሆነም ጠቁመዋል።
ይህ የጋዝጊብላ ወረዳ ፖሊስና የጸጥታ አካላት የፈጸሙት ጀግንነት፣ ለሌሎችም አካባቢዎች አርአያ የሚሆንና ሰላማችን በእጃችን ነው የሚለውን መልዕክት ዳግም ያረጋገጠ ተግባር ነው ሲሉም ኢንስፔክተር ግርማ እሸቴ
ገልጸዋል ።
የሁላችንም ንቃትና ትብብር የሀገርን ሰላም ለማስጠበቅ ብቸኛው መንገድ መሆኑን ይህ ክስተት ትልቅ ትምህርት ሰጥቷል ሲሉም ጠቁመዋል።








