የመኩሪያ ሰንደቅ የዋና ኢንስፔክተር አደፍርስ ታፈሰ ታማኝነትና የህሊና ዳኝነት።
ዩኒፎርሙ ባይናገር፣ ህሊናው ግን አወጋ፣
ጥቅም ሳያሸንፈው፣ ለሞራል የተጋ፤
ከጎዳናው የወደቀ፣ የሰው ላብና ጥረት፣
አደራ ነው ብሎ፣ አሳየን እውነት።
እጁ አልተንቀጠቀ፣ ለብር አልሳሳ፣
የህዝብን አደራ፣ በልቡ ያነገሰ ።
አደፍርስ ታፈሰ፣ የትውልድ አርአያ፣
ታማኝነት ማለት፣ ይሄ ነው መለኪያ!
በጥቅም በማይደለል ማንነት፣ በቅንነት እና በሙያ ስነ-ምግባር የታነጹት ዋና ኢንስፔክተር አደፍርስ ታፈሰ፤ በደሴ ከተማ ጎዳናዎች ላይ የፖሊስነትን ክብር ከፍ የሚያደርግ ደማቅ አርአያነት አሳይተዋል።
በደሴ ከተማ አስተዳደር ፖሊስ መምሪያ የትራፊክ አደጋ መከላከልና ቁጥጥር ክፍል ኃላፊ የሆኑት ዋና ኢንስፔክተር አደፍርስ፣ ጥር 28 ቀን 2018 ዓ.ም በመደበኛ የሥራ ተግባራቸው ላይ እያሉ ነበር ድንገት በጎዳና ላይ የወደቀ 25,400 (ሃያ አምስት ሺህ አራት መቶ) ብር ያገኙት።
መኮንኑ ያገኙትን ገንዘብ ለግል ጥቅማቸው ከማዋል ይልቅ፣ ለለበሱት የፖሊስ ዩኒፎርም ክብርና ለህዝብ አደራ በመገዛት ወዲያውኑ ለሚመለከተው አካል በማስረከብ የታማኝነት ተምሳሌት መሆናቸውን አስመስክረዋል።
ይህ ድርጊት ከገንዘብ ዝውውር ባለፈ ፖሊስ የገባውን ህዝብን በታማኝነት እና በኃላፊነት የማገልገል ቃልኪዳን የሚያሳይ ተግብር ፈጽመዋል።
የተቋሙን ክብር ከፍ ማድረግና የደሴ ከተማ ፖሊስ መምሪያን ስም በህዝብ ዘንድ ይበልጥ ጎልቶ እንዲታይ አድርገዋል።
ፖሊስ የህዝብ አለኝታና የታማኝነት ምንጭ መሆኑን በተግባር አሳይተዋል።
መኮነኑ የፈጸሙት በጎ ተግባር ለሌሎች የፖሊስ አባላትና አመራሮች የሞራል ልዕልና ከምንም በላይ መሆኑን ትልቅ ትምህርት ሰጥተዋል።
የለበስኩት ዩኒፎርም የህዝብ አደራ ነው የሚለውን መርህ በተግባር ያሳዩት ዋና ኢንስፔክተር አደፍርስ፣ በዘመናዊ የፖሊስ አገልግሎት ውስጥ ሊኖር የሚገባውን ታማኝ ተልዕኮ ፈፃሚነት በግልጽ አሳይተዋል።
የዋና ኢንስፔክተር አደፍርስ ታፈሰ ታማኝነት በቁሳቁስ በናወዘ ዓለም ውስጥ የሞራል ልዕልና ምን ማለት እንደሆነ በትልቅ ድምፅ ያስተማረ ክስተት በመሆኑ ክብር ይገባዎታል።
የእርስዎ ታማኝነት የሁላችንም ኩራት ነው።
ይህ ብር የጠፋባችሁ ግለሰብ፣ አስፈላጊውን ማስረጃ በመያዝ በደሴ ከተማ አስተዳደር ፖሊስ መምሪያ በአካል ቀርባችሁ በሕግ አግባብ መረከብ የምትችሉ መሆኑን መምሪያው ያስታውቃል።



