ለቻግኒ ከተማ ሰላም ዘብ በቆሙ የከተማዋ የፀጥታ አካላትና ማህበረሰብ ከፍተኛ ጥረት የተሻለ የሰላም ትሩፋት መገኘቱ ተገለፀ።
የከተማዋን ሰላም በዘላቂነት ለማስፈንም የከተመዋ የፀጥታ ኃይል ከሌሎች የጸጥታ ሀይሎች እና ከማህበረሰቡ ጋር ተቀናጅቶ እየሰራ እንደሆነ የከተማ አስተዳደሩ ፖሊስ ጽህፈት ቤት ገልጿል።
በአዊ ብሄረሰብ አስተዳደር ቻግኒ ከተማ የከተማዋ የፀጥታ አካላት ከማህበረሰቡ ጋር በሚያደርጉት የተቀናጀ የወንጀል መከላከልና የሰላም ማስጠበቅ በጎ ተግባር የተሻለ ሰላም መገኘቱን በአዊ ብሄረሰብ አስተዳደር ፖሊስ መምሪያ የቻግኒ ከተማ አስተዳደር ፖሊስ ፅህፈት ቤት አዛዥ ኮማንደር አገኘሁ ጥሩነህ ተናግረዋል።
ኮማንደር አገኘሁ ጥሩነህ እንደሚሉት ከተማዋ ከቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ጋር በቅርብ ርቀት የምትዋሰን እና ልዩ ልዩ የማህበረሰብ ክፍሎችን በሰፊው የምታስተናግድ ከመሆኗ ጋር ተያይዞ ከፍተኛ የንግድ ልውውጥ የምታስተናግድ ከተማ መሆኗንም ጠቁመዋል።
ለከተመዋ ሰላም ልዩ ትኩረት በመስጠት ወንጀልና ወንጀለኛን አስቀድሞ በመከላከል የከተማዋ ፖሊስ አባላት ከሌሎች የፀጥታ አካላትና ከማህበረሰቡ ጋር በመቀናጀት ተጨባጭ ስራ መሰራቱን ገልፀዋል።
ባለፉት ዓመታት በክልሉ ከተቀሰቀሰው ግጭት ጋር ተያይዞ በቻግኒ ከተማ ምንም ዓይነት የፀጥታ ችግር አልተፈጠረም ያሉት አዛዡ የከተማዋ ማህበረሰብ ሰላም ወዳድና ልማት ናፋቂ በመሆኑ ከፀጥታ አካላት ጋር በትብብር በመስራቱ መሆኑን አመላክተዋል።
የከተማዋ ፖሊስ ሰራዊት በወንጀል መከላከል፣በወንጀል ምርመራ፣በትራፊክ ቁጥጥር ስራ፣በኬላ ፍተሻ እና ሌሎች መደበኛና የኦፕሬሽን ተግባር ባከናወነው ብርቱ ስራ ባለፉት ስድስት ወራት የተሻለ ስራ ስለመሰራቱም ኮማንደር አገኘሁ ጥሩነህ ተናግረዋል።
ምክትል ኢንስፔክተር አለማየሁ ኀይሉ በከተማ አስተዳደሩ ፖሊስ ፅህፈት ቤት የማህበረሰብ ዐቀፍ ወንጀል መከላከል ክፍል ኃላፊ በበኩላቸው የከተማዋን ሰላም ዘላቂና አሰተማማኝ ለማድረግ ማህበረሰቡን ያሳተፈ የወንጀል መከላከል ስራ እየተሰራ ነው ብለዋል።
በጸጥታ ኃይሉ እና በማህበረሰቡ ቅንጅታዊ ስራ በከተመዋ ይፈጸሙ የነበሩ ወንጀሎች መቀነስ መቻሉን የገለፁት ምክትል ኢንስፔክተር አለማየሁ ኀይሉ ህገ ወጥነትን ከመከላከል አኳያም ባለፉት ስድስት ወራት በተደረኩ በርካታ የኬላ ፍተሻ ስራ የማህበረሰባችንን ሰላም ሊያውኩ የሚችሉ የተለያዩ በርካታ ተተኳሽ ጥይቶች፣ክላሾች፣የሽሻ ዕቃዎች እና ሌሎች ህገወጥ ነገሮች ከጥምር ጦሩ ጋር በመሆን መያዝ መቻላቸውን ገልፀዋል።
ለከተመዋ ሰላም መምጣት ከፍተኛ ሚና ለተጫወቱ የጸጥታ ኃይሎች እና ለነዋሪው ህዝብ በከተማ አስተዳደሩ ፖሊስ ጽህፈት ቤት ስም ምስጋና አቅርበዋል።










