የንጋት ጮራና የሰላም ዘብ የሆነው የ39ኛ ሻለቃ አድማ መከላከል ፖሊስ የጀግንነት ጉዞ ቀጥሏል።

የንጋት ጮራና የሰላም ዘብ የሆነው የ39ኛ ሻለቃ አድማ መከላከል ፖሊስ የጀግንነት ጉዞ ቀጥሏል።

እንደ አሸዋ በጎርፍ የማይወሰድ፣ እንደ ገለባም በለብ እሳት የማይዳፈን፤ ይልቁንም አቅሙን ከአለት፣ ወኔውን ደግሞ ከዱሩ ንጉስ አንበሳ ጋር ያስተካከለ ጀግና ምንጊዜም መዳረሻው ድል ነው።

የአማራ ክልል አድማ መከላከል ፖሊስም ይህንን እውነት በተግባር እየኖረው የሚገኝ፣ ራሱን እንደ ሻማ አቅልጦ ለህዝቡ ብርሃን የሚለግስ የንጋት ጮራ ሆኗል።

በአሁኑ ወቅት የግዳጅ ቀጠናውን በአዊ ብሄረሰብ አስተዳደር ያደረገው የ39ኛ ሻለቃ አድማ መከላከል ፖሊስ፣ የክልሉን ህዝብ ሰላምና ደህንነት ለማረጋገጥ አይተኬ ዋጋ እየከፈለ ይገኛል።

የሻለቃው አዛዥ ኮማንደር መኳንንት ታምራት ለዝግጅት ክፍላችን እንደገለጹት፤ ሰራዊቱ ግዳጁን በብቃት፣ በወኔና በስኬት ለመወጣት ቁርጠኛ እና በተልዕኮው ያመነ የህዝብ አለኝታ መሆኑን ገልጸዋል።

አዛዡ አክለውም የክልላችን ህዝብ ያጣው ሰላምና የመልካም አስተዳደር ጥያቄ በአስተማማኝ ሁኔታ ምላሽ እስኪያገኝ ድረስ፣ የህግ ማስከበር ስራችን ተጠናክሮ ይቀጥላል ሲሉ አረጋግጠዋል።

ሻለቃው ቀደም ሲል በታጣቂዎች ተይዘው የነበሩ በርካታ ቀጠናዎችን ነፃ በማድረግ፣ ማህበረሰቡ ወደ መደበኛ እንቅስቃሴው እንዲመለስ ከፍተኛ ድል ማስመዝገቡን ገልጸዋል።

የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ የጀመረው ስር ነቀል የሪፎርም ስራ በሰራዊቱ ዘንድ አዲስ የመነቃቃት መንፈስ ፈጥሯል ብለዋል።

ኮማንደር መኳንንት እንደሚያስረዱት፣ ይህ የለውጥ ጉዞ በአባላቱና በአመራሩ ዘንድ ከፍተኛ የሞራል ስንቅ በመሆኑ፣ ተቋሙን ከምንጊዜውም በላይ ለግዳጅ ዝግጁ አድርጎታል ብለዋል።

የሻለቃው አባላት በበኩላቸው፣ ከራስ ህይወት ይልቅ ለህዝብ ሰላም ዋጋ መክፈል ታላቅ ገድልና ኩራት መሆኑን ተናግረዋል።

ወታደር ማለት ሀገር ነው፤ ሀገር ያለ ወታደር ደግሞ ነፍስ እንደሌለው ስጋ ነው ያሉት የ39ኛ የአድማ መከላከል አባላት የአማራ ምድር የሰላም ጠባቂዎች በመሆናችን ከራስ በፊት ለህዝብ ሰላም ህይወታችንን እየሰጠን ሰላምን እናስከብራለን ብለዋል።

ህዝባችን በነፃነት ወጥቶ የመግባት፣ የመማርና የመልማት መብቱ እስኪረጋገጥ ድረስ ትግላችን አይቆምም ሲሉ አባላቱ ፅናታቸውን ገልጸዋል።

በመጨረሻም፣ የሻለቃው አመራሮችና አባላት ባስተላለፉት መልዕክት፤ ሰላም የዚህ ትውልድ ትልቅ ሀላፊነት በመሆኑ፣ የታጠቁ አካላት መንግስት ያቀረበውን የሰላም ጥሪ በመቀበል ወደ ማህበረሰቡ እንዲቀላቀሉ ጥሪያቸውን አቅርበዋል።

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Scroll to Top