በደብረ ታቦር ከተማ የተከበረው የቅዱስ መርቆሬዎስ አመታዊ የንግስ በዓል በሰላም ተጠናቀቀ

በደብረ ታቦር ከተማ የተከበረው የቅዱስ መርቆሬዎስ አመታዊ የንግስ በዓል በሰላም ተጠናቀቀ

በደብረ ታቦር ከተማ በድምቀት የተከበረው ዓመታዊው የቅዱስ መርቆሬዎስ ንግሥ በዓል፣ በሰላም እና በታላቅ መንፈሳዊ ሥነ-ሥርዓት መጠናቀቁ ተገልጿል።

በተከበረው የቅዱስ መርቆርዮስ የበዓል ስነስርዓት ላይ የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች፣የዞን አመራሮች ፣የሀይማኖት አባቶችና ጥሪ የተደረገላቸው እንነግዶች ታድመዋል።

በደብረ ታቦር ከተማ የተከበረው የቅዱስ መርቆርዮስ አመታዊ የንግስ በዓል፣ በማህበረሰቡ ንቁ ተሳትፎና በፀጥታ ኃይሉ ጠንካራ ጥበቃ ያለምንም የፀጥታ ችግር በድምቀት መጠናቀቁን የደብረ ታቦር ከተማ አስተዳደር ፖሊስ መምሪያ አዛዥ ኮማንደር ያለው ዘለቀ ገልጸዋል።

በዛሬው ዕለት በደብረ ታቦር ከተማ የተከበረው የቅዱስ መርቆርዮስ የንግስ በዓል የእምነት ስርዓት ብቻ ሳይሆን፣ ህዝብና መንግስት በጋራ ሲቆሙ የሚገኘውን የሰላም ትርፍ የታየበት መድረክ ሆኖ አልፏል ሲሉም አዛዡ አክለዋል።

የክልሉ የጸጥታ ኃይል እና ሌሎች የፀጥታ መዋቅሮች በመረጃ ልውውጥና በጋራ ስምሪት ያሳዩት አንድነት፣ የወንጀል ድርጊቶችን ቀድሞ በመከላከል ረገድ ውጤታማ ስራ እንዲከናወን አስችሏል ብለዋል።

የክልሉ የጸጥታ ኃይል ከሌሎች የፀጥታ አካላት ጋር የጋራ ዕቅድና ስምሪት አውጥቶ ውጤታማ ስራ ማከናወኑን የጠቀሱት አዛዡ

ወደ ከተማዋ መግቢያና መውጫ ኬላዎች ላይ ባከናወኑት ጥብቅ ፍተሻ፣ ማንኛውንም የጸጥታ ስጋት ቀድሞ መከላከል ተችሏል ብለዋል።

የፀጥታ ኃይሉ በበዓሉ ቦታና በከተማዋ የተለያዩ ቦታዎች ባደረገው የንቁ ጥበቃ ስራ፣ ምዕመናን ያለምንም ስጋት መንፈሳዊ ስነ-ስርዓታቸውን እንዲያከናውኑ ሆነዋል ብለዋል።

የደብረ ታቦር ከተማ ነዋሪዎች ከፀጥታ ኃይሉ ጎን በመቆም፣ ያልተለመዱ እንቅስቃሴዎችን በመጠቆም እና ከፀጥታ ኃይሉ ጎን ቆመው ወንጀልን ለመከላከል የነበራቸው ሚና ለበዓሉ ሰላማዊነት ዋነኛ ምሰሶ ነበሩ ሲሉም ገልፀዋል።

በከተማው የትራፊክ ፖሊስ አባላት በተደረገው ከፍተኛ ጥረት፣ በበዓሉ አካባቢ የነበረውን የሰውና የተሽከርካሪ መጨናነቅ ያለምንም የትራፊክ አደጋ እንዲስተናገድ በማድረግ የተሰጣቸውን ተልዕኮ በአግባቡ መወጣታቸውን ኮማንደር ያለው ዘለቀ ጠቁመዋል።

በዓሉ ያለምንም የፀጥታ ችግር እንዲጠናቀቅ ተልዕኳቸውን በብቃት ለተወጡ የፀጥታ አባላት፣ለሀይማኖት አባቶችና ለመላው የከተማዋ ነዋሪዎች በከተማ አስተዳደሩ ፖሊስ መምሪያ ስም የላቀ ምስጋና አቅርበዋል።

በተከበረው የቅዱስ መርቆርዮስ አመታዊ የንግስ በዓል ላይ ወንጀል መከላከልን አልፈው ለተፈፀሙ ወንጀሎች ፈጣን ፍትህ ለመስጠት ምርመራ፣ አቃቢ ህግ እና ፍርድ ቤት በጋራ ጊዜያዊ ችሎት አቋቁመው ውጤታማ ስራን ሰርተዋል ያሉት ደግሞ የአማራ ክልል ፖሊስ የግድያና ትራፊክ አደጋ ወንጀል ምርመራ መምሪያ ኃላፊ ኮማንደር ዘለቀ አይዳኙህም ናቸው ።

የምርመራ መዋቅሩ ከበዓሉ ቀናት አስቀድሞ የጀመረው በመረጃ የታገዘ የምርመራና የክትትል ስራ፣ በበዓሉ እለት ሊከሰቱ የሚችሉ ስጋቶችን ቀድሞ ለመለየት አስችሎታል ብለዋል።

የምርመራ ቡድኑ በህዝብ መሃል በመሰማራትና የመረጃ ምንጮችን በመጠቀም፣ በዓሉን ለወንጀል ተግባር ሊጠቀሙ ያሰቡ አካላትን እንቅስቃሴ በንቃት ሲከታተል መዋሉንም አክለዋል።

በኬላዎችና በተለያዩ የፍተሻ ጣቢያዎች ላይ በተደረጉ ምርመራዎች፣ ህገ-ወጥ ድርጊቶችንና አጠራጣሪ ቁሶችን በቁጥጥር ስር በማዋል ረገድ ውጤታማ ስራ ተሰርቷል ብለዋል።

በክልሉ በተቋቋመው ጊዜያዊ የችሎት ቦታዎች 2 ግለሰቦች የተለያየ ወንጀል ፈፅመው ስለተገኙ መዝገባቸው በአስቸኳይ ተጣርቶ ውሳኔ የተሰጠባቸው ሲሆን የፍርድ ውሳኔ መጠኑም ከስድስት ወር እስከ ሁለት አመት ቅጣት ተላልፎባቸዋል ሲሉም ኮማንደር ዘለቀ አይዳኙህም አረጋግጠዋል።

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Scroll to Top