በጠንካራ የእርስ በዕርስ ግንኙነት እና ማህበራዊ ህይወት የተገነባ ፖሊስ የማህበረሰብን አጋርነት መገንባት ይችላል ተባለ።
በማዕከላዊ ጎንደር ዞን ፖሊስ መምሪያ የምዕራብ ደንቢያ ወረዳ ፖሊስ ጽ/ቤት አመራሮችና አባላት የለአማራ ክልል ፖሊስ የጀመረዉን ሪፎርም ምሳሌ የሚሆን ስራን እየሰሩ እንደሚገኙ ተገልጿል።
የአማራ ህዝብን ታሪክ ለማኮሰስ ከውጭ ጠላቶቻችን ጋር ወግኖ የሚሰራውን ተላላኪ ቡድን ከመንግስት ጎን ቆማችሁ የአማራነት ስነልቦናን በመላበስ የክልሉን ሰላም ለመመለስ በቁርጠኝነት ከጠላት ጋር እየተፋለማችሁ የምትገኙ ጀግኖች ናችሁ ሲሉ የአማራ ክልል ፖሊስ ምክትል ኮሚሽነር እና የወንጀል መከላከል ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ምክትል ኮሚሽነር አበበ ውቤ ተናግረዋል።
በወረዳው ሰላም እንዲሰፍንና የልማት ስራዎች እንዲፋጠኑ ወደ ጫካ የወጡ ህገ-ወጥ ሀይሎችን በፅናት እየተፋለማችሁ ወረዳችሁን ባለማስደፈራችሁ የክልሉ ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ ይኮራባችሗል ብለዋል።
የህይወት መሰዋትነት የከፈላችሁበት ወታደራዊ ዝግጁነታችሁ የታየበት፣ ጀግንነታችሁ የተረጋገጠበት እና ፖሊስ ሁሌም ከህዝብ ጎን መሆኑን ያሳያችሁበት ጊዜ ነው ሲሉም አዛዡ ጠቁመዋል።
የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ የጀመረው የሪፎርም ስራ ወደ ወረዳ ወርዶ በተግባር ያየንበት በደንቢያ ወረዳ ፖሊስ ጽህፈት ቤት ነው ብለዋል።
የክልሉ ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ ከሌብነት የፀዳ፣በአዕምሮውም ሆነ በአካሉ የዳበረ የፖሊስ ሰራዊት ለመገንባት የለውጥ ስራዎችን እየተገበረ እንደሚገኝም ጠቁመዋል።
ለሰላም የሚከፈል ዋጋ ጥቅሙ ዘርፈ ብዙ እንደሆነ ተናግረው የአማራ ህዝብ ስቃይ እንዲቆም ህብረተሰቡ ከጸጥታ ኃይሉ ጎን ተሰልፎ ለሰላም ዘብ ሊቆም እንደሚገባም አሳስበዋል።
የክልሉ ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ የጀመረው የሪፎርም ስራ በሰራዊቱ ላይ መነሳሳትን የፈጠረ እና ወጥ የሆነ ፖሊሳዊ አስተሳሰብን የሚያጎለብት በመሆኑ እስከ ታች ድረስ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ጠቁመዋል።
የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ የኮሚዩኒኬሽንና ህዝብ ግንኙነት ኃላፊ ረዳት ኮሚሽነር ክንዱ ወንዴ በበኩላቸው የሰራችሁት ጀግንነት በሀገራችን በታሪክ መዝገብ ውስጥ በደማቁ ይጻፋል።
የክልሉ ሪፎርም በዚች ወረዳ ላይ ተግባራዊ በመሆኑ ሌሎች እየመጡ ተሞክሮ እንዲወስዱ እናደርጋለን ብለዋል።
ወታደር ብሔር እና ጎጥ እንደሌለው አስመስክራችኋል ያሉት ኃላፊው ፖሊሳዊ ስነ-ምግባርን ተላብሳችሁ በጀግንነት እና በቆራጥነት ጠላትን እየተፋለማችሁ ትገኛላችሁ ብለዋል።
በጠንካራ የእርስ በዕርስ ግንኙነት እና ማህበራዊ ህይወት የተገነባ ፖሊስ የማህበረሰቡን አጋርነት በቀላሉ መገንባት እንደሚችል በእናንተ አይተናል ሲሉም ኃላፊው አረጋግጠዋል።
የፖሊስ ሙያን ከሌሎች ሙያዎች የሚለየው የሰውን ህይወት መጠበቅና ሰላምን ማስፈን በመቻሉ ነው ፣ ቀጣይም የጀመራችሁትን አንድነትና ፍቅር አጠናክራችሁ በመቀጠል የተጣለባችሁን ኃላፊነት መወጣት ይኖርባችኋል ሲሉም አሳስበዋል።
የአማራ ክልል ፖሊስ ሰራዊቱን ለማዘመንና የተሳለጠ የወንጀል መከላከል ስራ መከወን የሚያስችል የለውጥ ስራ በመጀመረበት ማግስት የሪፎርም ስራውን በመተግበራችሁ ልንኮራ ይገባናል ብለዋል።
የምዕራብ ደንቢያ ፖሊስ በጀግንነትና በቆራጥነት ሰላምን እያስከበራችሁ የምትገኙ የክልሉ የልብ ትርታ ናችሁ ሲሉም አክለዋል።
የሀገር ሽማግሌዎች እና የሀይማኖት አባቶች የሰላም አስፈላጊነትን መስበክ ቀዳሚ ተግባራቸው በማድረግ ሰላም እንዲሰፍን መስራት አለባቸው ብለዋል።
የደንቢያ ወረዳ ፖሊስ ጽ/ቤት አመራሮች እና አባላት ከብሔር እና ጎጠኝነት የጸዳ ግንኙነት ያላቸው ፣ የተጠናከረ የማህበራዊ ህይወት ትስስርን ያዳበሩ የክልሉ ፖሊስ ምሳሌዎች ናቸው ያሉት ደግሞ የምዕራብ ደንቢያ ወረዳ ፖሊስ ጽህፈት ቤት አዛዥ ኢንስፔክተር የጸዳው ምስጋናው ናቸው።
ከሰሜኑ ጦርነት ጀምሮ እስካሁን ድረስ ወረዳውን ከጠላት ለመከላከል ምሽግ ሰርተው እየተፋለሙ ይገኛሉ ያሉት አዛዡ ለሰሯቸው ውጤታማ ስራዎች በዞኑ ሞዴል ፈፃሚ በመሆን የተለያዩ የማበረታቻ የምስክር ወረቀት እና ዋንጫዎች ሽልማት ማግኘት እንደቻሉም ገልፀዋል ።
ህገ-ወጥ ቡድኑ የፖሊስ ሰራዊቱን ከህብረተሰቡ ለመነጠል በርካታ የውሸት ፕሮፓጋንዳ ቢያናፍስም የፀጥታ ሀይሉ ግን የራሱን መረጃ በማደራጀት ህብረተሰቡ ወደ ፀጥታ ኃይሉ እንዲመለስ እና እምነት እንዲኖረው አድርገናል ብለዋል።
የምዕራብ ደንቢያ ወረዳ ፖሊስ ጽ/ቤት አመራሮችና አባላት ወረዳቸውን ለማውደም የመጣውን ጠላት ፊት ለፊት ተፋልመው ነፃ ያወጡ ለክልሉ ፖሊስ ምሳሌ የሚሆን የጀግንነት ተግባርን ፈፅመዋል ብለዋል።
የምዕራብ ደንቢያ ፖሊስ ሰላምን ለማስከበር ከጠላት ጋር ፊት ለፊት እየተዋጋ በሌላ በኩል ደግሞ ልማትን እያለማ ተቋሙን ያላስደፈረ ጀግና ሰራዊት ያለበት ነው ሲሉም አክለዋል።
የደንበያ ፖሊስ ጽህፈት ቤት ሰራተኞች ጠንካራ ጓዳዊ ፍቅርን የገነቡ ፣ በማህበራዊ ህይወታቸው የተሳሰሩ በመሆናቸው ከኪሳቸው ገንዘብ እያሰባሰቡ አቅመ ደካሞችን የሚረዱ ናቸው ሲሉም አዛዡ ተናግረዋል።
የማህበረሰብ አቀፍ የወንጀል መከላከል አሰራርን ለማህበረሰቡ በማስረፅ የሰላሙ ባለቤት እራሱ እንዲሆን በማድረግ እና የተቀናጀ የመረጃ ልውውጥ በመፍጠር ወረዳውን ከጠላት ነፃ ማድረግ ችለናል ብለዋል።
የሰውን ህይወት መጠበቅና ሰላምን ማስፈን ቀዳሚው ተግባራችን ነው ያሉት አዛዡ ቀጣይም የጀመርነውን አንድነትና ፍቅር አጠናክረን በመቀጠል የተጣለብንን ኃላፊነት ለመወጣት ዝግጁ ነን ብለዋል።
የምዕራብ ደንቢያ ፖሊስ ጽህፈት ቤት አባላት እንደገለጹት ፖሊስነት ሰበዓዊነትን ተላብሶ የሚሰራ የራሱን ጥቅም የማያስቀድም የተከበረ ስራ በመሆኑ ሙያው የሚፈቅደውን ስነምግባር ተላብሰን የህዝባችንን ሰላም እያስከበርን እንገኛለን ብለዋል።
ጠንካራ መሪ ሲኖር ጠንካራ ሰራተኛ ይኖራል ያሉት አባላቱ የፖሊስ ጽህፈት ቤታችን አመራሮች ቆራጥ ታግለው የሚያታግሉ ጀግና መሪዎች በመሆናቸው ከእነሱ ጎን ተሰልፈን አገር ሊያፈርስ የመጣን ህገ-ወጥ ቡድን በመፋለማችን ኩራት ይሰማናል ብለዋል ።
ፖሊሳዊ ስነ ምግባርን ተላብሰን፣ ጠንካራ ጓዳዊ ፍቅር ገንብተን አንድ አይነት ህዝብን የማገልገል አመለካከት በመገንባት ለሚፈጠሩት ችግሮች ሁሉ በጋራ እየተከላከልን እንገኛለን ብለዋል።
ጠንካራ የእርስ በዕርስ ግንኙነት እና ማህበራዊ ህይወት በመፍጠራችን በማህበረሰባችን ላይ እምነትን በመገንባት ከጎናችን ተሰልፎ ሰላሙን እንዲጠብቅ ማድረግ መቻላቸውንም ተናግረዋል።
ህግን ከማስከበር ጎን ለጎን ማህበረሰቡን አስተባብረን ብዙ የአቅመ ደካማ ቤቶችን ሰርተናል ሲሉም አክለዋል ።
ተቋሙ የጀመረውን የለውጥ ስራ አጠናክሮ ይቀጥልልን እንጂ እኛ ሰላምን ለማስከበር በጀግንነት እና በታማኝነት እንቆማለን ብለዋል።









