የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ የህዝብን ደህንነት ይበልጥ ለማረጋገጥ እና የወንጀል መከላከል ስራውን በቴክኖሎጂ በማስደገፍ የዜጎችን ተሳትፎ የማረጋገጥ አዲስ ዲጂታል አሰራር አስጀመረ።
የአማራ ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ ከኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ያስጀመረዉን የ የዜጎች ተሳትፎ መተግበሪያ (EFP app) የተሰኘው የሞባይል መተግበሪያ በክልል ደረጃ ስራ ላይ ማዋሉን አስታውቋል።
ይህ መተግበሪያ በፖሊስ እና በህብረተሰቡ መካከል ያለውን ግንኙነት በማጠናከር ረገድ አዲስ ምዕራፍ ይከፍታል ተብሎ ይጠበቃል።
የአማራ ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ ከኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ፣ ከአዲስ አበባ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ እና ከድሬ ደዋ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ ቀጥሎ በ3ኛደረጃ ነው የዜጎች ተሳትፎ መተግበሪያ (EFP App) አፑን በስራ ላይ እንዲውል ያደረገው።
በአሁኑ ወቅት የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ ወቅቱን የዋጀ የፖሊስ አገልግሎት ለመስጠትና የህዝብን ተሳትፎ ለማሳደግ ዘመናዊ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን በስፋት እየተጠቀመ ይገኛል። ከእነዚህም መካከል የዜጎች ተሳትፎ መተግበሪያ (EFP app) ዋናውና ተጠቃሽ ነው።
በአማራ ክልል ተግባራዊ እየተደረገ ያለው የየዜጎች ተሳትፎ መተግበሪያ (EFP app) ፖሊስ ከህብረተሰቡ ጋር ያለውን ግንኙነት በማሳለጥ ረገድ በተለይ በወንጀል መከላከል፣ በምርመራ እና በትራፊክ ቁጥጥር ረገድ ህብረተሰቡ መረጃ የመስጠት ተሳትፎን በማድረጉ ከፍተኛ ለውጥ እያመጣ ይገኛል።
የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ የዜጎች ተሳትፎ መተግበሪያን (EFP app) ተግባራዊ ማድረጉ፣ ተቋሙ ራሱን እያዘመነ መሆኑን የሚያሳይ ትልቅ እርምጃ ነው። ይህ ቴክኖሎጂ የወንጀል መከላከልና ለምርመራ ስራን ከባህላዊ አሰራር ወደ ዲጂታል በማሸጋገር፣ የህዝብን ደህንነት በአስተማማኝ ሁኔታ ለመጠበቅ የሚደረገውን ጉዞ ያፋጥነዋል።
አፕሊኬሽኑ በፖሊስና በህዝብ መካከል ያለውን ርቀት ቀንሶ ፈጣን፣ ውጤታማ እና ተቀባይነት ያለው የደህንነት አገልግሎት ማቅረብ ነው።
የዜጎች ተሳትፎ መተግበሪያ (EFP app ) በክልሉ በሚገኙ ሁሉም የዞን ፖሊስ መምሪዎች ጋር የተሳሰረ በመሆኑ የመረጃ ፍሰቱን በማፋጠን ቀጥተኛ ጥቅሞችን ያቀርባል።
በተለይም በክልሉ ሰላምና መረጋጋትን ለማስፈን በሚደረገው ጥረት የቴክኖሎጂ እገዛ ታክሎበት የፖሊስን ተአማኒነት ይገነባል ተብሎ ይታመናል።
መተግበሪያው በተለይ ወንጀልን አስቀድሞ በመከላከል እና መረጃዎችን በፍጥነት ለሚመለከተው አካል በማድረስ ረገድ ከፍተኛ ሚና ይጫወታል።
ማንኛውም ዜጋ ወንጀል ሲፈጸም ወይም የወንጀል ጥርጣሬ ሲኖርበት በአካል ፖሊስ ጣቢያ መገኘት ሳያስፈልገው ካለበት ቦታ ሆኖ መረጃ እንዲሰጥ ያስችላል።
መረጃ ሰጪዎች ማንነታቸው ሳይታወቅ ጥቆማዎችን ማድረስ የሚችሉበትን አስተማማኝ ስርዓት ዘርግቷል።
ፖሊስ ከህዝቡ የሚደርሱትን ጥቆማዎች በየደረጃው በሚገኙ የመረጃ ማዕከላት አማካኝነት በአጭር ጊዜ ውስጥ ተንትኖ ኦፕሬሽናል እርምጃ እንዲወስድ ይረዳል።
የየዜጎች ተሳትፎ መተግበሪያ (EFP app) ለአጠቃቀም ቀላል በሆነ መልኩ የተቀረጸ ሲሆን፣ ተጠቃሚዎች በስማርት ስልኮቻቸው ላይ በመጫን በቀላሉ ሊጠቀሙበት ይችላሉ።
ፖሊስ ተፈላጊ ወንጀለኞችን ፎቶና መረጃ በመተግበሪያው አማካኝነት ለህዝብ ሲያሳውቅ፣ ህብረተሰቡ
በመተግበሪያው ውስጥ የጥቆማ መስጫ ክፍል ውስጥ በመግባት ያዩትን ወይም የሰሙትን የወንጀል ድርጊት በጽሁፍ፣ በምስል፣ በድምጽ ወይም በቪዲዮ ጭምር ለፖሊስ መላክ ይችላሉ።
በመተግበሪያው የሚላኩ ጥቆማዎች የጂ-ፒ-ኤስ (GPS) መረጃን ስለሚያካትቱ፣ ፖሊስ የወንጀል ተጋላጭ የሆኑ ቦታዎችን ለይቶ ጥበቃውን እንዲያጠናክር ይረዳዋል።
ወንጀልን ለመከላከል የህዝብ ተሳትፎ ወሳኝ በመሆኑ ቀደም ሲል የነበሩት የመረጃ መቀበያ መንገዶች (በአካል መቅረብ ወይም በስልክ መደወል) የነበሩትን ውስንነቶች በከፍተኛ ሁኔታ መቅረፍ የሚያስችል ነው።
ይህ የየዜጎች ተሳትፎ መተግበሪያ (EFP app) መተግበሪያ እያንዳንዱን ዜጋ የፖሊስ አይንና ጆሮ በማድረግ፣ ወንጀለኞች የሚንቀሳቀሱበትን ምህዳር ያጠነክረዋል።
ከመጠን በላይ መጫን፣ ከፍጥነት በላይ ማሽከርከር ወይም የተከለከሉ ቦታዎች ላይ ማቆምን የመሳሰሉ ጥሰቶችን መንገደኞች ወይም እግረኞች ወዲያውኑ ፎቶ አንስተው ለትራፊክ ፖሊስ መላክ ይችላሉ።
ዋና ጠቅላይ መምሪያው የህብረተሰብ ተሳትፎ ማሳደጊያ አፑን ተግባራዊ የሚያደርጉ ብቁ የፖሊስ አባላትን ያሰማራ ሲሆን፣ ህብረተሰቡም መተግበሪያውን እንዴት መጠቀም እንዳለበት የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎችን እየሰራ ይገኛል።
ህብረተሰቡም ይህንን የዜጎች ተሳትፎ መተግበሪያ (EFP app) በስልኩ ላይ በመጫንና ትክክለኛ መረጃዎችን ለፖሊስ በማድረስ የዜግነት ድርሻውን እንዲወጣ ጥሪ ቀርቧል።





