“ፖሊስ የህዝብ አለኝታነቱን በተግባር እያሳየ ይገኛል” ኮሚሽነር ጀኔራል ዘላለም መንግስቴ (ዶ/ር)

“ፖሊስ የህዝብ አለኝታነቱን በተግባር እያሳየ ይገኛል” ኮሚሽነር ጀኔራል ዘላለም መንግስቴ (ዶ/ር)

የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ ለ2 ቀናት ያካሄደውን የ2018 ዓ.ም የ6 ወራት የሥራ አፈጻጸም ግምገማ በስኬት አጠናቋል።

በመድረኩ የተገኙ ስትራቴጂክ እና ከፍተኛ አመራሮች ለክልሉ ሰላም መከበር አዲስ የቁርጠኝነት መንፈስ አሳይተዋል።

በመድረኩም የክልሉን ሰላምና ጸጥታ ለማረጋገጥ የተከናወኑ ዋና ዋና ተግባራት፣ የተመዘገቡ ስኬቶች እና ያጋጠሙ ተግዳሮቶች ላይ ዝርዝር ውይይት ተደርጓል።

የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀኔራል ዘላለም መንግስቴ (ዶ/ር) በመድረኩ ላይ ባደረጉት ንግግር፣ የክልሉን ሰላምና ደህንነት ለማስጠበቅ የፖሊስ ሰራዊት እየከፈለ ያለውን መስዋዕትነት አድንቀዋል።

“ፖሊስ የህዝብ አለኝታነቱን በተግባር እያሳየ ይገኛል” ሲሉ ኮሚሽነር ጀኔራሉ አጽንኦት ሰጥተዋል።

ባለፉት ስድስት ወራት የክልላችንን ሰላም ለማረጋገጥና የህዝባችንን ደህንነት ለመጠበቅ በቁርጠኝነት ተሰርቷል ያሉት የፖሊስ አዛዡ የደረስንባቸው ስኬቶች የሰራዊታችንን ጥንካሬና የህዝባችንን ትብብር የሚያሳዩ ናቸው ሲሉ አክለዋል።

ወንጀልን ከመከላከል አኳያ አሁንም ትኩረት የሚሹ ጉዳዮች ስላሉ፣ በቀጣይ ስድስት ወራት የተጀመሩ የሪፎርም ስራዎችን በማጠናከርና የቴክኖሎጂ አጠቃቀማችንን በማሳደግ ለህዝባችን የተሻለ አገልግሎት መስጠት ይኖርብናል ብለዋል።

በሪፎርም ስራዎች ጠንካራ የአሰራር ስርዓት እና አደረጃጀት በመዘርጋቱ የሰራዊቱን ሞራል እና የስራ ተነሳሽነት በማሳደግ ለወንጀል መከላከል እና ለህግ ማስከበር ስራዎችን ያጠናከረ መሆኑን ኮሚሽነር ጀኔራሉ አስታውቀዋል።

በስድስት ወር የስራ አፈጻጸም ሪፖርቱ ላይ እንደተመለከተው፣ መምሪያው በበርካታ ዘርፎች ውጤታማ ስራዎችን አከናውኗል፦

በወንጀል መከላከል ባለፉት ስድስት ወራት በክልሉ አስተማማኝ ሰላም ለማስፈን በተደረገው ጥረት፣ ወንጀልን አስቀድሞ በመከላከል ረገድ አበረታች ውጤቶች መመዝገባቸው ተገልጿል።

ማህበረሰብ አቀፍ የፖሊስ አገልግሎትን በማጠናከር፣ ህዝብን ያሳተፈ የጥበቃና የደህንነት ስራዎች ተከናውነዋል። ይህም በክልሉ የሚስተዋሉ የወንጀል ድርጊቶችን በመቀነስ ረገድ ከፍተኛ ድርሻ እንደነበረው ተጠቁሟል።

በክልሉ የተከናወኑ ህዝባዊ እና ሐይማኖታዊ በዓላትን እንዲሁም ዓለምአቀፍ፣ ሀገር አቀፍ እና ክልላዊ ሁነቶች በሰላም እንዲከበሩ የፖሊስ ሰራዊቱ ከፌዴራል እና ከክልሉ የጸጥታ ኃይሎች ጋር የፈጸመው ተግባር አኩሪ መሆኑ ተነግሯል።

የአማራ ክልል ፖሊስ ከክልሉ እና ከፌደራል የጸጥታ እና ደኅንነት ግብረ-ኃይል ጋር በቅንጅት በመሆን ለህገወጥ ታጣቂዎች ሊደርሱ የነበሩ በርካታ የጦር መሳሪያዎች እና ተተኳሾችን በቁጥጥር ስር ማዋሉ ተገልጿል።

ህዝባዊ መሠረት ያለው የጸጥታ ሥራ በማከናወን የወንጀል ስጋቶችን መቀነስ መቻሉም በስድስት ወር የስራ አፈጻጸም ሪፖርቱ ተገልጿል።

በወንጀል ምርመራ በኩልም በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የታገዘ የምርመራ ስልቶችን በመጠቀም፣ ውስብስብ የሆኑ የወንጀል መዝገቦችን በአጭር ጊዜ እና በሙያዊ ብቃት በማጣራት ለፍትህ አካላት ተደራሽ የማድረግ ስራ በስኬት ተከናውኗል።

በህገ-ወጥ የመሬት ወረራና በመንግስት ንብረት ምዝበራ የተጠረጠሩ በርካታ መዝገቦች ተጣርተው ለፍትህ አካላት ተልከዋል።

የፎረንሲክ ምርመራ ቴክኖሎጂዎች እና አዳዲስ የተጠርጣሪ ማቆያ ክፍሎች ግንባታ ለምርመራ ስራው ጥራት ትልቅ ግብዓት መሆናቸው ተገልጿል።

የወንጀል ምርመራ ስራ ከግምት ይልቅ በበቂ ማስረጃ፣ በሳይንሳዊ መንገድ እና በፍትሐዊነት ሊከናወን እንደሚገባ አጽንኦት ተሰጥቷል።

ፖሊስ ከህዝብና ከመንግስት የተጣለበትን አደራ ለመወጣት የሙያ ስነ-ምግባርን የተላበሰ የምርመራ ስርዓት መዘርጋቱን አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ተመልክቷል።

በአስተዳደር እና ልማት በኩልም የፖሊስ ሰራዊቱን አቅም ለመገንባትና በስነ-ምግባር የታነጸ ኃይል ለመፍጠር የተጀመሩ የሪፎርም ስራዎች ውጤት እያሳዩ መሆናቸው ተገልጿል።

በየደረጃው ላሉ የፖሊስ አመራሮች የስራ ላይ ስልጠና በመስጠት እና ውጤታማ የአመራር ምደባ በመከናወኑ ይታዩ የነበሩ የአሰራር ክፍተቶችን እና የፍትሐዊነት ጥያቄዎችን መመለስ መቻሉ ተገልጿል።

ዩኒቨርሲቲ ኮሌጁ ሰራዊቱን በዕውቀትና በክህሎት ለማብቃት እያከናወነ ያለው የማሰልጠን ተግባር ተጠናክሮ ቀጥሏል።

የሰራዊቱን የአስፈጻሚነት አቅም ለመገንባት በተግባር ላይ ያተኮሩ ስልጠናዎችን ሲሰጥ ቆይቷል።

ይህም ሰራዊቱ በስነ-ምግባር የታነጸና ለህዝብ አገልጋይነት ዝግጁ እንዲሆን በማድረግ ረገድ ቁልፍ ሚና እየተጫወተ እንደሚገኝ በሪፖርቱ ተመላክቷል።

በተለይም በልዩ ልዩ የሙያ መስኮች የሚሰጡ ስልጠናዎች የፖሊስን ሙያዊ ብቃት ወደ ላቀ ደረጃ አሸጋግረዋል።

የአማራ ክልል ፖሊስ የኮሙኒኬሽንና ህዝብ ግንኙነት ዋና መምሪያ፣ ተቋሙ በህዝብ ዘንድ ያለውን ቅቡልነት ለማሳደግ በርካታ ስራዎች በስኬት ተከናውነዋል።

በቀረበው ሪፖርት ላይ እንደተመለከተው፣ በዋናነት የሚከተሉት ስራዎች በስኬት ተከናውነዋል፡-

የፖሊስ ሚዲያ የሰራዊት አባላት እያከናወኑ ያሉትን ተግባራት ለህዝብና ለሰራዊቱ ተደራሽ በማድረግ በኩል ሰፊ ስራዎች ተሰርተዋል።

በክልሉ የሚከናወኑ ልዩ ልዩ ሁነቶችን በማድመቅና በማጀብ ረገድ የፖሊስ ማርች ባንድና የኪነት ቡድን የላቀ አፈጻጸም አሳይተዋል።

ፖሊስ በህዝብ ዘንድ የሚታመንና የዜጎችን ሰላም በታማኝነት የሚያስጠብቅ ተቋም መሆኑን የሚገልጽ በርካታ የህዝብ ግንኙነት ስራዎች በትኩረት ተሰርተዋል።

በአጠቃላይ የኮሙኒኬሽን ስራው የሰራዊቱን ገጽታ ለመገንባትና ከህዝብ ጋር ያለውን ግንኙነት ለማጠናከር ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑ በሪፖርቱ ተመላክቷል።

የውይይቱ ተሳታፊዎች በበኩላቸው ይህ ግምገማ የፖሊስ ተቋሙን የአመራር ብቃት ወደ ላቀ ደረጃ የሚያሸጋግርና ለክልሉ ዘላቂ ሰላም ተስፋ የሚሰጥ መሆኑ አስታውቀዋል።

‘የሕዝባችን ሰላም ቀዳሚ ተግባራችን ነው’ ያሉት አመራሮቹ፣ የሕዝቡን የሰላም ጥማት ለማርካትና የደኅንነት ስጋቶችን ለመቀነስ በቅንጅት እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል።

አመራሮቹ የክልሉን ወቅታዊ ተጨባጭ ሁኔታ ከግምት ውስጥ ያስገቡ አዳዲስ የፀጥታ ስልቶችን ተግባራዊ ለማድረግ መግባባት ላይ ደርሰዋል።

በግምገማው ላይ የተሳተፉ ስትራቴጂክ እና ከፍተኛ የፖሊስ አመራሮች በቀጣይ የክልሉን ሕዝብ ሰላምና ደኅንነት በአስተማማኝ ሁኔታ ለመጠበቅ የላቀ ትኩረት ሰጥተው እንደሚሠሩ ቃል ገብተዋል።

በመድረኩ ላይ የክልሉ ፖሊስ ዋና አዛዥ ኮሚሽነር ጀኔራል ዘላለም መንግስቴ (ዶ/ር) እና ምክትል ኮሚሽነሮች በግምገማው ወቅት ለተነሱ መሠረታዊ ጥያቄዎችና ስጋቶች ዝርዝር ማብራሪያ ሰጥተዋል።

በዚህም በየዘርፋቸው የታዩ ክፍተቶችን መነሻ በማድረግ፣ በቀጣይ ስድስት ወራት ሊተገበሩ የሚገቡ የክንውን ስልቶችን ለአመራሩ አጋርተዋል።

ይህ የአመራሮች ማብራሪያና የተቀመጠው አቅጣጫ የክልሉን ፖሊስ ኦፕሬሽናዊ ዝግጁነት ይበልጥ እንደሚያጠናክረው ተገልጿል።

ከቀጣይ የትኩረት አቅጣጫዎች መካከልም፦

የተጀመረውን የሪፎርም ስራ አጠናክሮ ማስቀጠል፤

በህግ ማስከበር ተልዕኮ የመፈፀም ብቃትን ማሳደግ፤

የማህበረሰብ ዐቀፍ ፖሊስ አገልግሎት አሰራሮችን ተደራሽ ማድረግ፤

ጠንካራና ፍትሃዊ የወንጀል ምርመራ ስራን ማከናወን፤

የሎጀስቲክስ አስተዳደር እና ተደራሽነት ስርዓትን ማረጋገጥ፤

የመረጃና ክትትል ስራን በማዘመን የተቋሙን ብቃት ማሳደግ፤

ለሚዲያና ህዝብ ግንኙነት ስራ ላይ ትኩረት መስጠት፤

ሰባተኛው ሀገር ዓቀፍ ምርጫ በሰላማዊ መንገድ እንዲጠናቀቅ በልዩ ትኩረት መስራት የሚሉት ዋና ዋናዎቹ ናቸው።

በመጨረሻም በልዩ ልዩ ግዳጆች ለተሰማሩ የክልሉ ፖሊስ ሰራዊት፣ ለሀገር መከላከያ ሰራዊት፣ ለፌዴራል ፖሊስ እንዲሁም ለክልሉ ሚሊሻ እና ሰላም አስከባሪ አካላት በተሰራው ስራ እና በተመዘገበው አኩሪ ድል ክልሉ ከገጠመው ቀውስ በመታደግ እና ዘላቂ ሰላም ማስፈን በመቻሉ በእኔና በተቋሙ ስም ምስጋና አቀርባለሁ ሲሉ ኮሚሽነር ጀኔራል ዘላለም መንግስቴ (ዶ/ር) አስታውቀዋል።

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Scroll to Top