“ጥምቀት የሰላም የፍቅር፣የአንድነታችንና የጥንካሬያችን መገለጫ ነው!”
ኮሚሽነር ጀኔራል ዘላለም መንግሥቴ (ዶ/ር) የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና አዛዥ ለከተራና ለጥምቀት በዓል ያስተላለፉት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት
የጥምቀት በዓል የሰላም፣ የፍቅር፣ የትሕትናና የአንድነት ተምሳሌት ነው። ይህ በዓል በመላ በሀገራችን ኢትዮጵያ በልየኡ ሁኔታ በክልላችን በታላቅ ድምቀት፣ በባህላዊ እሴቶችና በሀይማኖታዊ ስርዓቶች ተጠብቆ የሚከበር ሲሆን፣ የአለም አቀፍ ቅርሳችን ጭምር መገለጫም ነው።
ለመላው የክርስትና እምነት ተከታዮች እንዲሁም የጥምቀት በዓልን በታላቅ ጉጉት ለምትጠባበቁ የክልላችንና የሀገራችን ህዝቦች በሙሉ፦
በአማራ ክልል ፖሊስ እና በራሴ ስም እንኳን ለ2018 ዓ.ም የከተራና የጥምቀት በዓል በሰላም አደረሳችሁ ለማለት እወዳለሁ።
የጥምቀት በዓል በዓለም አቀፍ ደረጃ በዩኔስኮ የተመዘገበ የማይዳሰስ ቅርስ ከመሆኑም በላይ፣ እኛ ኢትዮጵያውያን የምንታወቅበትን የእንግዳ ተቀባይነት፣ የወንድማማችነት እና የታላቅ ባህል መገለጫ ነው።
ይህ በዓል ከሀይማኖታዊ እሴቱ ባሻገር፣ በመላው ክልላችን የሚገኙ የቱሪስት መዳረሻዎቻችን በደመቀ ሁኔታ የሚታዩበትና ህዝባችን በአንድነት ቆሞ ጥንካሬውን የሚያሳይበት ዕለት ነው።
ውድ የክልላችን ነዋሪዎችና የበዓሉ ታዳሚዎች፤ በዓሉ በሰላምና በደስታ ተጀምሮ እንዲጠናቀቅ የአማራ ክልል ፖሊስ ከሌሎች የፌደራል እና የክልል የጸጥታ ግብር-ኃይል ጋር በመቀናጀት አስፈላጊውን የጸጥታ ጥበቃ ለማድረግ በሙሉ አቅሙ ዝግጅቱን አጠናቆ ወደ ስራ ገብቷል።
በበዓሉ አከባበር ወቅት የሚከተሉትን ነጥቦች ትኩረት እንድትሰጡ አሳስባለሁ፦
ፖሊስ የህዝብ አለኝታ ነው። ህብረተሰቡ በየአካባቢው ለተሰማሩ የጸጥታ አካላት አስፈላጊውን መረጃ በመስጠትና ለፍተሻ ስራዎች ትብብር በማድረግ እንደተለመደው የዜግነት ድርሻውን እንዲወጣ ጥሪዬን አቀርባለሁ።
በበዓሉ ስነ-ስርዓት ላይ በሚፈጠሩ ከፍተኛ የሰዎች ስብስቦች ውስጥ ሰላም አደፍራሾችና አጋጣሚውን የሚጠባበቁ የወንጀል ድርጊት ፈጻሚዎች እንዳይሳካላቸው ንቁ መሆን ያስፈልጋል።
ስለሆነም ማንኛውንም አጠራጣሪ እንቅስቃሴ ሲመለከቱ በአቅራቢያዎ ለሚገኝ የፖሊስ አባል ወይም በስልክ መስመሮቻችን እንዲያሳውቁ እናሳስባለን።
ወደ ጥምቀተ ባህር የሚደረጉ ጉዞዎችና የትራፊክ እንቅስቃሴዎች ሰላማዊ እንዲሆኑ አሽከርካሪዎችና እግረኞች የትራፊክ ደንቦችን በአግባቡ እንዲያከብሩ፣ በተለይም ከመጠን በላይ ፍጥነትና መጠጥ ጠጥቶ ማሽከርከርን በመከላከል የሰው ህይወትና ንብረትን በመጠበቅ ሊሆን ይገባል።
ይህ በዓል የፍቅርና የመቻቻል በዓል እንደመሆኑ፣ እንግዶቻችንን በፍቅር በመቀበልና የተቸገሩትን በመርዳት የክልላችንን መልካም ስም እንድናስጠራ አደራ እላለሁ።
በመጨረሻም፣ የከተራና የጥምቀት በዓል በታላቅ መንፈሳዊነትና በሰላም ተከብሮ እንዲጠናቀቅ የክልላችን ፖሊስ እና አጋር የፌደራል እና የክልላችን የጸጥታ ኃይሎች ሌሊትና ቀን በቁርጠኝነት እንደሚሰሩ በድጋሚ ላረጋግጥላችሁ እወዳለሁ።
በድጋሚ እንኳን ለብርሃነ ጥምቀቱ በሰላም አደረሳችሁ በዓሉ የሰላም፣ የጤና እና የደስታ ይሁንልን!
በጀግንነት መጠበቅ፤ በሰብዓዊነት ማገልገል!
ኮሚሽነር ጀኔራል ዘላለም መንግሥቴ (ዶ/ር)
የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና አዛዥ
ጥር 2018 ዓ.ም
ባህር ዳር፣ ኢትዮጵያ

