የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ ከፍተኛ አመራሮች ግዳጅ ላይ የሚገኙ የፀጥታ አባላትን ጉብኝት አድርገዋል።
የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ ምክትል ኮሚሽነር እና የወንጀል መከላከል ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ምክትል ኮሚሽነር አበበ ውቤ እና ሌሎች ከፍተኛ አመራሮች በተገኙበት በእንፍራንዝ ከተማ የ10ኛ ሻለቃ እና በጎርጎራ የ8ኛ ሻለቃ በምሽግ ላይ የሚገኙ የአድማ መከላከል አባላትን በቦታው ተገኝተው ጎብኝተዋል።
የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ ምክትል ኮሚሽነር እና የወንጀል መከላከል ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ምክትል ኮሚሽነር አበበ ውቤ የክልሉ ህዝብ በሰላም ወጥቶ እንዳይገባ በማድረግ ማህበራዊ ህይወቱን እያቃወሱ የሚገኙ ህገ-ወጥ አካላትን ለመከላከል የክልሉ ፖሊስ ሰራዊት በሁሉም የክልሉ አካባቢዎች ከሌሎች የጸጥታ አካላት ጋር በመጣመር ሰላምን እያስከበረ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
አንድ አይነት አስተሳሰብ እና ተልዕኮ ተላብሳችሁ የክልሉን ህዝብ ደህንነት ማስከበር የምትችሉ ጀግኖች በመሆናችሁ ኮርተንባችኋል ብለዋል።
ሰላምን ለሚፈልገው ህዝብ በታማኝነት እና በጀግንነት ማገልገል ኩራት ነው ያሉት አዛዡ ጓዳዊ ፍቅራችሁን በማጠናከር የክልሉ ህዝብ የጣለባችሁን አደራ ከዚህ በበለጠ መወጣት ይኖርባችኋል ብለዋል ።
ያለችን አንድ ሀገር ስለሆነች የትኛውም ዜጋ በፈለገበት ቦታ በነፃነት የመንቀሳቀስ፣ ንብረት የማፍራት እና የተረጋጋ ማህበራዊ ህይወትን መምራት እንዲችል ማድረግ ይጠበቅብናል ብለዋል።
ወታደራዊ ዲሲፕሊን አና የዕዝ ሰንሰለት በማክበር የሚሰጠጡ ተልዕኮዎችን ተቀብሎ ለመፈፀም ዝግጁ መሆን እንደሚኖርባቸውም አሳስበዋል።
የትኛውም ሀገርን ሊያፈርስ እና አንድነትን ሊበትን የሚመጣን ሀይል መተኪያ የሌላት ህይወታችሁን አስይዛችሁ በጀግንነት ከጠላት ጋር እየተፋለማችሁ የምትገኙ ጀግኖች ናችሁ ያሉት ደግሞ የአማራ ክልል ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ የኮሚዩኒኬሽን እና ህዝብ ግንኙነት ዋና መምሪያ ኃላፊ ረዳት ኮሚሽነር ክንዱ ወንዴ ናቸው።
በክልሉ በስራው የሚያምን አላማ ያለው ጀግና ሰራዊት እየተገነባ እንደሆነም እናንተ ምሳሌዎች ናችሁ ብለዋል።
የክልሉ ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ
ሰራዊቱ ወጥ የሆነ አመለካከት እንዲኖረው እየሰራ ያለው የለውጥ ስራ ሰራዊቱን የሚያነቃቃ እና ፍቅርን የሚያጨር አንደሆነም ጠቁመዋል።
የ10ኛ እነ የ8ኛ ሻለቃ አድማ መከላከል አመራር እና አባላት በበኩላቸው የህዝባችንን ሰላም ለማረጋገጥ በገባነው ቃልኪዳን መሠረት የሚሰጠንን ተልዕኮ እየተወጣን እንገኛለን ብለዋል።
የወጣንበት አላማ የህዝባችንን ሰላም ማስጠበቅ እስከሆነ ድረስ አንድነታችንን በማጠናከር ኃላፊነታችንን እንወጣለንም ብለዋል።
የተሰጠንን ግዳጅ በብቃት እና በጀግንነት እየተወጣን እንገኛለን ያሉት የአድማ መከላከል አባላት በህልውናችን የሚመጣ የትኛውም አካል ለመመከት በተጠንቀቅ ላይ እንገኛለን ብለዋል ።
ጽናታችንን እና ጀግንነታችንን አጠናክረን በመቀጠል የክልላችንን ብሎም የሀገራችንን ሰላም ማስጠበቅ ቀዳሚው ተግባራችን ነው ብለዋል።
የአማራ ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ እየከወነ ያለው የለውጥ ስራ ለሰራዊቱ ከፍተኛ መነሳሳት እና እምነትን እየፈጠረ እንደሚገኝም ጠቁመዋል።
የክልሉን ሰላም ለማስከበር ጠላትን ፊት ለፊት እየተፋለመ እና ህይወቱን እየሰጠ የሚገኘው የክልሉ የፀጥታ ሀይል በሰራዊቱ ላይ የሚታዩ የመልካም አስተዳደር ችግሮች ክልሉ ፈጣን መፍትሔ መሰጠት እንደሚኖርበትም ጠቁመዋለ።












