“በሰሜን ሸዋ ዞን የተገኘውን ሰላም ዘላቂ ለማድረግ የወንጀል መከላከል እና የተቀናጀ የኦፕሬሽን ስራዎች ተጠናክሮ ይቀጥላል!” ኮማንደር ንጉሴ ሞገስ

“በሰሜን ሸዋ ዞን የተገኘውን ሰላም ዘላቂ ለማድረግ የወንጀል መከላከል እና የተቀናጀ የኦፕሬሽን ስራዎች ተጠናክሮ ይቀጥላል!” ኮማንደር ንጉሴ ሞገስ

በሰሜን ሸዋ ዞን ላለፉት ወራት የህዝቡን ደኅንነት እና የዜጎችን ሰላማዊ እንቅስቃሴ ለማረጋገጥ የጸጥታ ኃይሉ ቀንና ሌሊት ባከናወነው የተቀናጀ የወንጀል መከላከል ስራ በአሁኑ ወቅት በዞኑ አስተማማኝ ሰላም መስፈኑን የዞኑ ፖሊስ መምሪያ አስታውቋል።

የሰሜን ሸዋ ዞን ፖሊስ መምሪያ አዛዥ ኮማንደር ንጉሴ ሞገስ በሰጡት ማብራሪያ በዞኑ የነበሩ የጸጥታ ስጋቶችን በዘላቂነት ለመፍታት እና የህዝቡን ሰላም ለማረጋገጥ የመከላከያ ሰራዊት፣ የፌደራል ፖሊስ፣ የክልል ፖሊስ እና ሌሎች የጸጥታ አካላት በጋራ መሥራታቸውን አንስተዋል።

ይህ የተቀናጀ ስራ በአካባቢው ላይ ተጋርጦ የነበረውን ስጋት በመቀልበስ ረገድ ከፍተኛ ውጤት ማስመዝገቡንም ገልጸዋል።

የአማራ ክልል ፖሊስ ሪፎርም ማካሄዱን ተከትሎ በሰሜን ሸዋ ዞን ፖሊስ የተከናወኑ ውጤታማ የወንጀል መከላከል ስራዎች የህዝቡን ሰላም እና ደኅንነት ያረጋገጡ መሆናቸውንም አዛዡ ጨምረው አብራርተዋል።

እንደ አዛዡ ገለጻ የጸጥታ አካላት በከፍተኛ መስዋዕትነት የወሰዱት እርምጃ የዜጎችን የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ ወደ ቀድሞ ሁኔታው መመለስ አስችሏል።

የጸጥታ ኃይሉ የህዝብን ደኅንነት ለማስጠበቅ መስዋዕትነት እየከፈለ ነው ያሉት ኮማንደር ንጉሴ የጸጥታ ኃይሉ “የህዝብ ሰላም የእኛ ድል ነው!” በሚል መሪ ቃል መልከዓ ምድራዊ እና የአየር ንብረት አስቸጋሪነት ሳይበግረው በዱር በገደሉ ተሰማርቶ የሰላም ስራውን ሲያከናውን ቆይቷል ሲሉ አብራርተዋል።

አዛዡ አክለውም የዞኑ ፖሊስ ሰራዊት ከአጋር የጸጥታ ኃይሎች ጋር በቅንጅት ቀን ከሌት በሰሩት ስራ ዛሬ ላይ ህዝቡ ያለምንም ስጋት የዕለት ተዕለት ተግባሩን እንዲያከናውን አስችለናል ብለዋል።

በተለይም በሰሜን ሸዋ ዞን ያለውን የደኅንነት ሁኔታ አስመልክቶ ሲያስረዱ ቀደም ሲል የትራንስፖርት እንቅስቃሴ ላይ ይፈጠሩ የነበሩ ስጋቶች በአሁኑ ወቅት ሙሉ በሙሉ መወገዳቸውን እና መንገዱ ክፍት ሆኖ አገልግሎት እየሰጠ መሆኑን አስታውቀዋል።

ሰላሙ መረጋገጡን ተከትሎ በዞኑ የሚገኙ የኢንዱስትሪ መንደሮች፣ የንግድ ተቋማት እና የግብርና ስራዎች በሙሉ አቅማቸው ወደ ስራ መመለሳቸውን ነው የዞኑ ፖሊስ አዛዥ አክለው ያብራሩት።

“ሰላም ከሌለ ልማት የለም!” የሚሉት ኮማንደር ንጉሴ በመሆኑም የጸጥታ ኃይሉ የወሰደው እርምጃ ለዞኑ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ መነቃቃት ትልቅ መሰረት ጥሏል ብለዋል።

የጸጥታ ኃይሉ በከተማም ሆነ በገጠር ቀበሌዎች ቀንና ሌሊት ባደረገው የተቀናጀ የኦፕሬሽን ተግባር ስጋት የነበሩባቸው አካባቢዎች ነጻ መሆናቸውም ተገልጿል።

በሰሜን ሸዋ ዞን እና አካባቢው የሚገኙ የኢንቨስትመንት ተቋማት ሰላማዊ በሆነ ሁኔታ ምርታቸውን እያመረቱ እንደሚገኙም ተጠቁሟል።

ለተገኘው የሰላም ውጤት የአካባቢው ማህበረሰብ ላበረከተው አስተዋጽኦ ከፍተኛ ምስጋና ያቀረቡት ኮማንደር ንጉሴ ህዝቡ መረጃ በመስጠትና የጥፋት ኃይሎችን በማጋለጥ ረገድ ከጸጥታ ኃይሉ ጎን መቆሙን ጠቅሰዋል።

ህዝቡ የሰላም ባለቤት መሆኑን በተግባር አሳይቷል፤ ይህ ቅንጅት ደግሞ ለቀጣይ ስራዎቻችን ትልቅ ጥንካሬ ነው ሲሉም የዞኑ ፖሊስ አዛዥ አክለው ተናግረዋል።

የዞኑ ፖሊስ መምሪያ የተገኘውን ሰላም ዘላቂ ለማድረግ እና በየትኛውም አቅጣጫ የሚነሱ የሰላም ጠንቆችን ለመከላከል አሁንም በከፍተኛ ዝግጁነት ላይ እንደሚገኝም አጽንኦት ሰጥተው ገልጸዋል።

ህዝቡም ጥቆማ በመስጠት እና አካባቢውን በመጠበቅ ረገድ የጀመረውን ትብብር አጠናክሮ እንዲቀጥል የዞኑ ፖሊስ አዛዥ ጥሪ አቅርበዋል።

በመጨረሻም የጸጥታ ኃይሉ የህዝብን ደህንነት አደጋ ላይ የሚጥሉ ማናቸውንም ሙከራዎች በንቃት እየተከታተለ እርምጃ መውሰዱን እንደሚቀጥል እና ለሰላሙ መረጋገጥ የሚከፈለውን መስዋዕትነት ሁሉ ለመክፈል ዝግጁ መሆናቸውን ኮማንደር ንጉሴ ሞገስ የሰሜን ሸዋ ዞን ፖሊስ መምሪያ አዛዥ አረጋግጠዋል።

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Scroll to Top