በተለያዩ አካባቢዎች ታጥቀው ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ህገ-ወጥ አካላት የሰላም ጥሪን በመቀበል ወደ ማህበረሰቡ መቀላቀላቸውን አጠናክረው ቀጥለዋል።
በደቡብ ጎንደር ዞን በላይ ጋይንት ወረዳ መኳቢያና ግድም አካባቢ ታጥቀው ሲንቀሳቀሱ የነበሩ የሃይል አማራጭ ተከታዮች፣ መንግስትና ህዝብ ያቀረቡላቸውን የሰላም ጥሪ በመቀበል ወደ ሰላማዊ ህይወት መመለሳቸው ተገልጿል።
የአካባቢው የሀገር ሽማግሌዎችና የሃይማኖት አባቶች በቦታው ተገኝተው ከፍተኛ አቀባበል ያደረጉ ሲሆን፣ ታጣቂዎቹም ከነሙሉ ትጥቃቸው ወደ ሰላማዊ ህይወታቸው በይፋ ተቀላቅለዋል።
በዕለቱ ንግግር ያደረጉት አመራሮች፣ የሰላም አማራጭን መምረጥ ለሀገር እድገትና ለህዝብ መረጋጋት ያለውን ፋይዳ በመጥቀስ፣ ወደ ሰላማዊ ህይወት የተመለሱት አካላት ለወሰዱት ቁርጠኛ ውሳኔ ምስጋና አቅርበዋል። በአሁኑ ወቅትም ለገቡት ታጣቂዎች በከተማው አስተዳደር አማካኝነት ደማቅ አቀባበል እየተደረገላቸው እንደሚገኝ ገልጸዋል።
የሰላም አማራጭን ተቀብለው የገቡ ታጣቂዎች ተሰልፈው የቆዩበት የትግል መስመር የተሳሳተ እና ሕዝብን ያጎሳቆለ መኾኑን ተናግረዋል። ይህን በመረዳት የቀረበውን የሰላም አማራጭ መቀበላቸውን ገልጸዋል።
ታጣቂዎቹ ለተደረገላቸዉ አቀባበል ምስጋና አቅርበዋል። ሌሎች ታጣቂዎችም የሰላምን አማራጭ እንዲቀበሉ ጥሪ አቅርበዋል።
በተመሳሳይ ዜና በሰሜን ሸዋ ዞን መንግሥት ያቀረበውን የሰላም ጥሪ የተቀበሉ ታጣቂዎች በደብረ ብርሃን ከተማ ወደ ሰላም መጥተዋል።
በዞኑ የተለያዩ ወረዳዎች በጫካ ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ህገ-ወጥ ታጣቂዎች የክልል እና የዞን ከፍተኛ መሪዎች፣ የመከላከያ ሠራዊት ከፍተኛ መኮንኖች፣ የሃይማኖት አባቶች እና የሀገር ሽማግሌዎች በተገኙበት ትጥቃቸውን በማስረከብ ወደሰላማዊ ኑሯቸው ተመልሰዋል።




