የደብረ ብርሃን ከተማ የሰላም አየር እየተነፈሰች ነው!
የደብረ ብርሃን ከተማ ፖሊስ መምሪያ ህብረተሰቡን በሰላም ስራው ላይ በንቃት እንዲሳተፍ በማድረጉ በከተማዋ ተጨባጭ ሰላም መምጣቱንም አስታውቋል።
የደብረ ብርሃን ከተማ ፖሊስ መምሪያ አዛዥ ኮማንደር ገብረ መስቀል ቦጋለ በከተማዋ የተመዘገበው ውጤት የመነጨው በፖሊስና በህዝብ መካከል ካለው ጠንካራ መተማመን መሆኑን አስረድተዋል።
እንደ ደብረ ብርሃን ከተማ የፖሊስ መምሪያ አዛዥ ገለጻ የከተማዋን ሰላም በዘላቂነት ለማረጋገጥ ‘ሰላሜ በእጄ ነው’ በሚል መርህ ህብረተሰቡን በየሰፈሩ አደራጅተናል።
ፖሊስ ብቻውን ሰላምን ማስፈን አይችልም ያሉት የፖሊስ አዛዡ ህዝቡ ግን መረጃ በመስጠት እና በፓትሮል ስራው ላይ በቀጥታ በመሳተፍ ወንጀለኞች የሚንቀሳቀሱበት ቀዳዳ እንዲዘጋ አድርጓል ብለዋል።
እንደ ደብረብርሃን ከተማ ፖሊስ አዛዥ ገለጻ በኢንዱስትሪ መንደሮችና በንግድ ተቋማት አካባቢ ያለው ስጋት መቀነሱ፣ ያልተገቡ እንቅስቃሴዎችን በቁጥጥር ስር በማዋል እና በህዝቡ ዘንድ የመረጋጋት ስሜት መፍጠሩ ተጨባጭ ውጤት ታይቶበታል።
አሁን ላይ በከተማዋ የትኛውም አካባቢ የሌሊት የፓትሮል ስራው ተጠናክሮ ቀጥሏል ሲሉም የደብረብርሃን ከተማ ፖሊስ አዛዥ ኮማንደር ገብረ መስቀል ቦጋለ አክለው ተናግረዋል።
ምክትል ኮማንደር አባይ ሙሉነህ የከተማው የወንጀል መከላከል ምክትል መምሪያ ኃላፊ በበኩላቸው ሰላምን በጋራ የመጠበቅ ባህላችን ለውጥ አምጥቷል፤ የከተማዋን ጸጥታ ለማደፍረስ የሚሞክሩ አካላትም የመንቀሳቀሻ ቀዳዳ አጥተዋል ብለዋል።
ቀደም ሲል ይስተዋሉ የነበሩ የጸጥታ ስጋቶች በህዝብና በፖሊስ የተቀናጀ ስራ መቃለላቸውን ምክትል ኮማንደር አባይ አረጋግጠዋል።
የሌሊት ጥበቃ ስራው ከተጀመረ ወዲህ የስርቆት እና ሌሎች ልዩ ልዩ የወንጀል ድርጊቶች በከፍተኛ ሁኔታ መቀነሳቸውን ነው ምክትል ኮማንደር አባይ ያብራሩት።
በከተማዋ የእምዬ ምንሊክ ክፍለ ከተማ ነዋሪ የሆኑት አቶ አበበ ካሳሁን እንዲህ ይላሉ፦ “ቀደም ሲል በሌሊት ወጥቶ መንቀሳቀስ ቀርቶ በቤታችን ተኝተንም ስጋት ነበረብን። አሁን ግን ከፖሊስ ጋር በመሆን በየተራ ሰፈርን መጠበቅ ከጀመርን ወዲህ ሰላማችን ተመልሷል። ወጣቱ፣ ጎልማሳውና ፖሊስ እጅና ጓንት ሆነው በመስራታቸው የከተማችን ድባብ ተቀይሯል።”
ሌላዋ የአፄ ዘርዓያዕቆብ ክፍለ ከተማ ነዋሪ ወይዘሮ አሰገደች ወልደ ፃዲቅ በበኩላቸው የንግድ ስራቸው በሰላም እንዲቀጥል የጥበቃ ስራው ትልቅ እገዛ ማድረጉን ጠቅሰው፣ ሰላምን በጋራ መጠበቅ እንደሚቻል በተግባር እያየን ነው ብለዋል።
አስተያየታቸውን የሰጡ የከተማዋ ነዋሪዎች፣ የሌሊት የፓትሮል ስራው የከተማዋን የንግድና ማህበራዊ እንቅስቃሴ ወደ ቀድሞ ሁኔታው እንዲመለስ ትልቅ ሚና ማበርከቱን ገልፀዋል።
ይህ በደብረ ብርሃን የተጀመረው የተቀናጀ የጥበቃ ስራ በሌሎችም አካባቢዎች እንደ አርአያ የሚወሰድ መሆኑ ተጠቁሟል።
ይህ አደረጃጀት ይበልጥ ተጠናክሮ የሚቀጥል ሲሆን፣ ህብረተሰቡ ለሚያደርገው ያልተቆጠበ ትብብር የከተማው ፖሊስ ምስጋና አቅርቧል።
በቀጣይም አጠራጣሪ ነገሮች ሲገጥሙ ፈጣን መረጃ በመስጠት ሰላምን በጋራ የመጠበቁ ስራ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ ቀርቧል።
“አሁን በሰላም ተኝተን እናድራለን!” የሚለው የብዙዎች ምስክርነት መሆኑን በስፍራው ተገኝተን ለማረጋገጥ ችለናል።









