“አላማችን አደጋን መቀነስ ብቻ ሳይሆን የዜጎችን ደህንነት ማረጋገጥ ነው!”
በትራፊክ አደጋ የሚከሰትን የሞት መጠን በ50 በመቶ ለመቀነስ ያለመ የተቀናጀ ስልጠና ተሰጠ።
የፌደራል የመንገድ ደህንነት እና መድን ፈንድ አገልግሎት፣ ከክልል የትራንስፖርት ዘርፍ ከፍተኛ አመራሮች፣ ከፖሊስ አመራሮች፣ ከሚዲያ አመራሮች፣ ከሀይማኖት አባቶች እንዲሁም ከልዩ ልዩ የማህበረሰብ ክፍሎች ጋር በመሆን በትራፊክ ህግ ማስከበር እና በድህረ-አደጋ ምላሽ አሰጣጥ ላይ ያተኮረ ከፍተኛ ስልጠና በደብረብርሃን ከተማ ተሰጥቷል።
ስልጠናው በዋናነት ትኩረቱን ያደረገው በተሻሻለው የትራፊክ ህግ ማስከበር ስርአት፣ በቴክኖሎጂ የታገዘ ቁጥጥር እና አደጋ ከተከሰተ በኋላ የሚሰጥ ፈጣን የህክምና እና የፅኑ እርዳታ ድጋፍ ላይ ነው።
አቶ መሀመድ ሀሰን የፌደራል የመንገድ ደህንነት እና መድን ፈንድ ምክትል ዋና ስራ አስፈጻሚ በስልጠናው መክፈቻ ላይ ባደረጉት ንግግር የትራፊክ አደጋ በሀገሪቱ ኢኮኖሚ እና ማህበራዊ መስተጋብር ላይ እያደረሰ ያለው ጉዳት ከፍተኛ መሆኑን ገልጸዋል።
ዓለማቀፍ ተሞክሮዎችን በመውሰድ እንደ ሀገር በተመረጡ የትራፊክ አደጋ በሚበዛባቸው አካባቢዎች በትራፊክ አደጋ ምክንያት የሚመዘገብን የሞት መጠን በ50 በመቶ ለመቀነስ የሚያስችል እንቅስቃሴ ተግባራዊ እየተደረገ መሆኑንም አብራርተዋል።
ይህን ለማሳካት ደግሞ የህግ ማስከበር ስራው ከባህላዊ አሰራር ወጥቶ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የታገዘ መሆን አለበት ሲሉ ምክትል ዋና ስራ አስፈጻሚው ተናግረዋል።
የትራፊክ አደጋ ከተከሰተ በኋላ ባሉት ወሳኝ ደቂቃዎች ውስጥ ለተጎጂዎች የሚደረገው የህክምና እርዳታ አሰጣጥ ላይ የተቀናጀ አሰራር መዘርጋት ለነገ የሚባል ስራ እንዳልሆነ አስገንዝበዋል።
ጋሻው አወቀ (ዶ/ር) የአማራ ክልል የመንገድ ትራንስፖርት እና ሎጀስቲክ ቢሮ ኃላፊ በበኩላቸው ስልጠናው በክልል ደረጃ ያለውን የትራፊክ ደህንነት ችግር ለመቅረፍ ያለውን ፋይዳ አብራርተዋል።
በአማራ ክልል የሚታየውን የትራፊክ አደጋ ስጋት ለመቀነስ በየደረጃው ያሉ የትራፊክ ህግ አስከባሪዎችን አቅም መገንባት ወሳኝ ነው ብለዋል።
“አላማችን አደጋን መቀነስ ብቻ ሳይሆን የዜጎችን ደህንነት ማረጋገጥ ነው!” ሲሉ ጋሻው አወቀ (ዶ/ር) የአማራ ክልል የመንገድ ትራንስፖርት እና ሎጀስቲክ ቢሮ ኃላፊ በአጽንኦት ተናግረዋል።
አደጋዎች ሲከሰቱ የሚሰጠው ምላሽ አሁንም ክፍተቶች ያሉበት በመሆኑ፣ ከጤና ዘርፍ ጋር ተቀናጅቶ መስራት ለውጥ ያመጣል ያሉት የቢሮ ኃላፊው ክልሉ ይህንን የተቀናጀ ስርዓት ለመተግበር ሙሉ ዝግጁነቱን ያረጋግጣል ብለዋል።
እንደ ጋሻው አወቀ (ዶ/ር) ገለጻ የትራፊክ ደህንነት ስራ የአንድ ተቋም ብቻ ሳይሆን የባለድርሻ አካላት የተቀናጀ ጥረት ውጤት ነው።
በአማራ ክልል የህግ ማስከበር ስራውን በማጠናከር እና አደጋ ሲከሰት ፈጣን ምላሽ የሚሰጡ አካላትን በማቀናጀት የዜጎቻችንን ህይወት ለመታደግ ቁርጠኛ ነን ሲሉ ጋሻው አወቀ (ዶ/ር) አክለው አብራርተዋል።
ይህ ስልጠናም በዘርፉ ያሉ አስፈጻሚ አካላትን አቅም በመገንባት ረገድ ከፍተኛ እገዛ ያደርጋል ሲሉ ጋሻው አወቀ (ዶ/ር) የአማራ ክልል የመንገድ ትራንስፖርት እና ሎጀስቲክ ቢሮ ኃላፊ ገልጸዋል።
በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የታገዘ የህግ ማስከበር ስርዓት በመዘርጋት እና አደጋ ሲከሰት የሚሰጠውን የህክምና እርዳታ በማዘመን፣ ሊተርፉ የሚችሉ ህይወቶችን መታደግ አለብን ያሉት ደግሞ ረዳት ኮሚሽነር ክንዱ ወንዴ የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ የኮሙኒኬሽንና ህዝብ ግንኙነት ዋና መምሪያ ኃላፊ ናቸው።
አሽከርካሪዎች ህግን እንዲያከብሩ የግንዛቤ ስራ ብቻ ሳይሆን፣ ጥብቅ እና ተከታታይነት ያለው የቴክኖሎጂ ቁጥጥር ስራ ላይ መዋል አለበት ሲሉ አክለው አስገንዝበዋል።
የሚዲያ እና የህዝብ ግንኙነት ባለሙያዎች የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርቶችን በመስጠት ኃላፊነታቸውን ሊወጡ ይገባል ሲሉ ረዳት ኮሚሽነር ክንዱ ወንዴ የኮሙኒኬሽንና ህዝብ ግንኙነት ዋና መምሪያ ኃላፊ አሳስበዋል።
የውይይቱ ተሳታፊዎች በበኩላቸው በክልሉ በተለይም በከፍተኛ የትራፊክ ፍሰት በሚታይባቸው ኮሪደሮች ላይ ጥብቅ ቁጥጥር ሊደረግ እንደሚገባ ጠቁመዋል።
አብዛኛው ተጎጂ ህይወቱ የሚያልፈው ወደ ጤና ተቋም በሚደረግ ጉዞ ላይ በመሆኑ፣ በመንገድ ዳር የሚገኙ የጤና ጣቢያዎች ለአደጋ ተጎጂዎች ልዩ ትኩረት የሚሰጡበት አሰራር ሊጠናከር ይገባል ሲሉ የስልጠናው ተሳታፊዎች አጽንኦት ሰጥተው አሳስበዋል።
በዘርፉ ከፍተኛ ባለሙያዎች እና አመራሮች ልዩ ልዩ ሰነዶች እና ጥናቶች ቀርበው ውይይት የተካሄደባቸው ሲሆን ስልጠናው ለሁለት ቀናት የሚሰጥ መሆኑ የተገኘው መረጃ ይጠቁማል።














