ቀጣይ ለሚከበሩ የገና እና የጥምቀት በዓላትን ያለምንም የጸጥታ ችግር እንዲከበሩ የጸጥታ ሀይሉ ከፍተኛ ዝግጅት ማድረጉ ተገለጸ።
የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ በ2018 ዓ.ም የሚከበሩትን የገና እና የጥምቀት በዓላት በሰላም እንዲከበሩ የሚያስችል ልዩ የበዓል እቅድ ውይይት ከፀጥታ ግብረ-ሀይሉ ጋር አድርጓል ።
የአማራ ክልል ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ ምክትል ኮሚሽነርና የወንጀል መከላከል ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ምክትል ኮሚሽነር አበበ ውቤ የወጣው ዕቅድ አሁን ያለውን የክልሉን የፀጥታ ችግር ግምት ውስጥ ያስገባ
በዓላትን ለማክበር ወደ ክልሉ የሚመጣውን ህዝብ ለመጠበቅ እና ሰላሙ እንዲረጋገጥ የሚያስችል መሆኑን ገልፀዋል ።
በባላት ወቅት ዘረፋ ፣ግድያ፣ ህገ-ወጥ ጥይት ተኩስ እና ህገ-ወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውርን ለመከላከል ህብረተሰቡን የጸጥታው ባለቤት በማድረግ ቅንጅታዊ አሰራርን አጠናክሮ መስራት የሚያስችል ልዩ እቅድ መሆኑንም ጠቁመዋል።
በዓሉን ለማክበር ከውጭ እና ከአገር ውስጥ ወደ ክልሉ በርካታ እንግዶች ስለሚመጡ ለመጡበት ዓላማ ያለምንም መሳቀቅና ፍርሐት አክብረው እንዲመለሱ የፀጥታ ኃይሉ በትኩረት ለመስራት በቂ ዝግጅት ማድረጉንም ጠቁመዋል።
እንደ ምክትል ኮሚሽነር አበበ ውቤ ገለፃ የወንጀል ድርጊት ይፈጸምባቸዋል ተብለው በሚጠረጠሩ ተቋማትና ሆቴሎች አካባቢ የቅድመ ወንጀል መከላከል ስራ በመስራት የበዓሉ ታዳሚዎች በሰላም እንዲያከብሩ ማድረግ የጸጥታ ኃይሉ ኃላፊነት በመሆኑ በትኩረት እየሰራን እንገኛለን ብለዋል ።
በዓላት በሰላም እንዲከበሩ የተዋቀረ የፀጥታ ግብረ ኃይል ስላለ ችግሮች በሚከሰቱበት ወቅት ጊዜያዊ መፍትሄ እንዲሰጥና ሊከሰቱ የሚችሉ ወንጀሎችን የቅድመ መከላከል ስራ እንዲከናወን አቅጣጫ እንደሚሰጥም ምክትል ኮሚሸነር አበበ ጠቁመዋል።
ታቦታት በሚያርፉበት አካባቢ ችግር እንዳይፈጠር ከበጎ ፈቃደኛ ወጣቶች ጋር በመቀናጀት ከፍተሻ ጀምሮ የጸጥታ ኃይሉ የራሱን የወንጀል መከላከል ዘዴዎች ተጠቅሞ ምንም አይነት ችግር እንዳይፈጠር ማድረግ የሚያስችል ቁመና ላይ እንደሚገኝም ምክትል ኮሚሽነሩ ገልፀዋል።
ጸረ ሰላም ኃይሎች ችግር ፈጥረው በዓሉን እንዳያደናቅፊ የመረጃ ልውውጣችንን በማጠናከር ቀድሞ መከላከል ቀዳሚው ተግባራችን ሊሆን ይገባል።
የአማራ ክልል ፖሊሰ ዋና ጠቅላይ መምሪያ የህብረተሰቡን ሰላም ለማረጋገጥ እና በዓላት በሰላም እንዲከበሩ ከሌሎች የጸጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት ሌት ተቀን እየሰራ እንደሚገኝም ምክትል ኮሚሽነር አበበ ውቤ ጠቁመዋል።
የባህር ዳር ከተማ አስተዳደር ፖሊስ መምሪያ አዛዥ ኮማንደር ዋለልኝ ቢምረው በዓሉ ተጀምሮ እስኪጠናቀቅ ድረስ ምንም አይነት የፀጥታ ችግር ሳይፈጠር እንዲከበር የፀጥታ ኃይላችን በቂ ዝግጅት አድርጓል ብለዋል።
በርካታ የውጭ እና የአገር ውስጥ ቱሪስቶች በዓሉን ለመታደም ስለሚመጡ የጸጥታ ቸግር እንዳይገጥማቸው ከማህበረሰቡ እና ከሀይማኖት አባቶች ጋር ውይይት አድርገናል ያሉት አዛዡ በዓላት ሰላማዊ ሆነው እንዲጠናቀቁ ከወትሮው በተለየ ዝግጅት ለማድረግ የሚያስችል ልዩ የበዓል ዕቅድ ውይይት ላይ እንገኛለን ብለዋል።
በዓላት በሚከበሩበት ጊዜ የሀሰተኛ የብር ኖት ፣የእንስሳት ስርቆት፣ የነጋዴዎች ያልተገባ የዋጋ ጭማሪ እንዳይፈጠር የጸጥታ ኃይሉ ከህብረተሰቡ እና አጋር የፀጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት መስራት የሚያስችል የበዓል እቅድ መደረጉን ጠቁመዋል።
አሁን ያለውን ሀገራዊ እና የክልል የጸጥታ ሁኔታ በመረዳት የሚከበሩ በዓላት በሰላም እንዲጠናቀቁ ከሌሎች የጸጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት ተልኳችንን መወጣት ይኖርብናል ሲሉም ኮማንደር ዋለልኝ ቢምረው ተናግረዋል።
የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ የልዩ ተቋማትና መሰረተ ልማት ፖሊስ የ1ኛ ሻለቃ አዛዥ ኮ/ር ሙሉ መለሰ ዛሬ የተወያየንበት እቅድ ቀጣይ ለሚከበሩት የገና እና የጥምቀት በዓላት በሰላም እንዲከበሩ ለማድረግ የቅድመ ወንጀል መከላከል ስራ ስምሪትን የሚያጠናክር ልዩ የበዓል እቅድ ውይይት ነው ብለዋል።
ለወንጀል ተጋላጭ ናቸው ብለን የምንገምታቸውን ተቋማትና ቦታዎች በመለየት ልዩ ጥበቃ እያደረግን እንገኛለን ያሉት አዛዡ ከማህበረሰቡ ጋር በመቀናጀት የተፋጠነ የመረጃ ልውውጥን ተግባራዊ በማድረግ የፀጥታ ችግር እንዳይፈጠር ተጠናክረን እንሰራለን ብለዋል።
እነዚህ በዓላት በሚከበሩበት ወቅት ችግሮች እንዳይፈጠሩ ማህበረሰቡ እራሱን የፀጥታው ባለቤት በማድረግ መከላከል እንዳለበትና ከአቅሙ በላይ የሆኑ ሁነቶች ሲፈጠሩም በአካባቢው ለሚገኝ የፀጥታ ኃይል መረጃ መስጠት ይኖርባቸዋል ብለዋል።











