በአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ እና በዘመን ኮንስትራክሽን ኮርፖሬሽን መካከል የጀግኖች ማዕከል ግንባታ የውል ስምምነት ሰነድ ተፈረመ።

በአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ እና በዘመን ኮንስትራክሽን ኮርፖሬሽን መካከል የጀግኖች ማዕከል ግንባታ የውል ስምምነት ሰነድ ተፈረመ።

የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ በደብረ ብርሃን ከተማ ለሚያስገነባው የአካል ጉዳት ለሚደርስባቸው የክልሉ ፖሊስ ሰራዊት ማገገሚያነት የሚውል የጀግኖች ማዕከል ግንባታ ከዘመን ኮንስትራክሽን ኮርፖሬሽን ጋር የሁለቱ ተቋማት ከፍተኛ ኃላፊዎች በተገኙበት የግንባታ ውል ስምምነት ተፈራርመዋል።

የስምምነት ሰነዱን የተፈራረሙት የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ ምክትል ኮሚሽነርና የአስተዳደርና ልማት ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ረዳት ኮሚሽነር አያልነህ ተስፋዬ እንደገለጹት የጀግኖች ማዕከል ግንባታ ዋና ዓላማ በተለያየ ምክንያት ጉዳት ለሚደርሰባቸው የአማራ ክልል ፖሊስ አባላት ማገገሚያነት እና ከባድ ጉዳት ለደረሰባቸው አባላትም የተለያዩ የሙያ ስልጠና የታገዘ የስራ ዕድል እንዲያገኙ ለማስቻል ነው ብለዋል።

እንደ ረዳት ኮሚሽነር አያልነህ ተስፋዬ ገለፃ ግንባታው ራሳችን በራሳችን በሚል መርህ የክልሉ ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ክቡር ኮሚሽነር ዘላለም መንግስቴ(ዶ/ር)በቅርቡ ካስመረቁት “የምርጫ ደህንነትና የፀጥታ ተቋማት ሚና”ከተሰኘው መፅሀፍ የሽያጭ ገቢና ከሁሉም የፖሊስ ሰራዊት ደመወዝ መዋጮ በዋናነት የሚገነባ ሲሆን ከክልሉ መንግስት ድጋፍ እና ከተለያዩ የገቢ ማሰባሰቢያ ፕሮግራሞች መታቀዱንም አብራርተዋል።

ዘመን ኮንስትራክሽን ኮርፖሬሽን ዘመኑን የዋጀ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን የሚጠቀም ድርጂት ነው ያሉት ምክትል ኮሚሽነሩ ግንባታውን በፍጥነት እና በጥራት ገንብቶ ለአገልግሎት ክፍት እንደሚያደርግልን በማመን እንደ ተቋም አብሮ ለመስራት የሚያስችለንን የውል ስምምነት ለመፈራረም ችለናል ብለዋል ።

ረዳት ኮሚሽነር አያልነህ ተስፋየ አክለውም የጀግኖች ማዕከል ግንባታ ከኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ በመቀጠል ግንባር ቀደሙ ፕሮጀክት መሆኑን ጠቁመዋል።

የሰራዊቱን ግዳጅ የመፈፀም ዓቅም የሚያጠናክርና የሞራል ልዕልናን የሚያጎለብት የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ የሪፎርም አንዱ አካል መሆኑንም አብራርተዋል።

የዘመን ኮንስትራክሽን ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈፃሚ

አቶ ታደሰ ግርማ በበኩላቸው ድርጅታችን ፍጥነት እና ጥራትን የሚያሳልጡ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን በመጠቀም ግንባር ቀደም በመሆኑ ከክልሉ ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ ጋር የምናደርገውን የውል ስምምነት የግንባታ ስራ ለመፈፀም ያስችለናል ብለዋል።

ለህዝባችን ሰላምና ለሀገር ደህንነት ሲሉ የህይወት እና የአካል ጉዳት መስዕዋትነት እየከፈሉ ለሚገኙት የክልሉ የፖሊስ አባላት ማገገሚያነት የሚውል የጀግኖች ማዕከል ግንባታን ለመገንባት ውል በመቀበላችን ደስታችን ወደር የለውም ብለዋል።

ግንባታውን በባለቤትነት ስሜት ተቀብለን ደረጃውን በጠበቀ መልኩ ገንብተን ለማስረከብ ቃል አንገባለን ሲሉም ተናግረዋል።

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Scroll to Top