የፈለገ ሕይወት አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ለአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ የህክምና ቁሳቁስ ድጋፍ አደረገ።

የፈለገ ሕይወት አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ለአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ የህክምና ቁሳቁስ ድጋፍ አደረገ።

የአማራ ክልል ጤና ቢሮ እና ፈለገ ሕይወት አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የፖሊስ ስራዊቱን ጤና ለማስጠበቅ የሚያግዙ የህክምና መገልገያ ቁሳቁሶችን ለአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ ድጋፍ አድርጓል።

የተደረገውን የህክምና ቁሳቁስ ድጋፍ የተረከቡት የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ ምክትል ኮሚሽነርና የአስተዳደር እና ልማት ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ረዳት ኮሚሽነር አያልነህ ተስፋዬ ፖሊስ ተሻጋሪ እና ተወዳዳሪ ተቋም ለመገንባት በሚደረገው የሪፎርም ስራ ወቅት ድጋፉ መደረጉ በጤናው ዘርፍ ክፍተቶችን ለመሙላትና ጤናማና ግዳጁን በብቃት መወጣት የሚችል ሰራዊት ለመገንባት ጉልህ ፋይዳ ይኖረዋል ብለዋል።

ህይዎቱን እየሰጠ ለሚገኘው ፖሊስ ሰራዊት ጤናውን መጠበቅ የተቋሙ ትልቅ ኃላፊነት በመሆኑ የፖሊስ ተቋሙን ጤና ጣቢያ ወደ ሆስፒታል ለማሳደግ እንቅስቃሴዎች መጀመራቸውን ተናግረዋል፡፡

ከፖሊስ ሰራዊቱ በተጨማሪም ለማህበረሰቡ የህክምና አገልግሎት ለመስጠት ዕቅድ መኖሩንም ረዳት ኮሚሽነር አያልነህ ተስፋዬ ጠቁመዋል።

የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ የጤና አገልግሎት መምሪያ ኃላፊ ኮማንደር መሰለ ስዩም በበኩላቸው የተደረገው ድጋፍ የሰራዊታችንን የጤና ሁኔታ ለማሻሻልና ጤና ጣቢያውን ወደ ሆስፒታል ለማሳደግ የተያዘውን ተቋማዊ ዕቅድ የሚያግዝ በመሆኑ ቀጣይነት እንዲኖረውና እስከ ታች ድረስ ተደራሽ ሊሆን እነደሚገባውም አመላክተዋል።

የህክምና ቁሳቁሱን ያስረከቡት የአማራ ክልል ጤና ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ አበበ ተምትሜ የክልሉ ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ በጤናው ዘርፍ እያካሄደ ያለው የሪፎርም ስራ ለክልሉ ጤና ቢሮ እንደ ተሞክሮ ሊወሰድ የሚገባ ነው ብለዋል፡፡

የሰራዊቱን ጤና ለማረጋገጥ እና ተደራሽነትን ለማስፋት የሚያስችል በመሆኑ በጤናው ዘርፍ ያሉ ክፍተቶችን ለቅረፍ የሚያግዝ ድጋፍ እንደሚሆንም ጠቁመዋል።

በክልሉ ጤና ቢሮ እና በፖሊስ ተቋም መካከል ያለው ትብብር ተጠናክሮ ይቀጥላል ያሉት ምክትል ቢሮ ኃላፊው ጤናማ የሆነ የፖሊስ ሰራዊት ለመፍጠር የክልሉ ጤና ቢሮ ከህክምና ቁሳቁስ በተጨማሪም የሙያተኛ አቅም ግንባታ ስልጠና በመስጠት ተገቢውን ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውንም አስታውቀዋል።

የፈለገ ሕይወት አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ስራ አስኪያጅ አቶ አብይ ፍስሐ በበኩላቸው ፖሊስ ተቋሙ እያደረገ ያለው የለውጥ ስራ ለሌሎች ተቋማት በምሳሌነት ሊጠቀስ የሚገባ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

የክልሉን ሰላም ለመጠበቅ እየከፈለ ካለው መስዕዋትነት ጋር ተያይዞ ጉዳት ለሚደርስባቸው የሰራዊት አባላት የተሻለ የህክምና አገልግሎት እንዲያገኙ ለማስቻል ቅንጅታዊ ስራችን ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

የክልሉን ሰላም ለማምጣት ፖሊስ የላቀ ስራ እያከናወነ ይገኛል ያሉት አቶ አብይ ፍስሐ ለፖሊስ ሰራዊቱ ጤናማነት መረጋገጥ እና የተሟላ የህክምና አገልግሎቶችን ለመስጠት ሆስፒታሉ ድጋፉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።

ማይክሮስኮፕ፣ ተኝቶ መታከሚያ አልጋ፣ ኦክስጅን፣ ስቴቶስኮፕ፣ ኬሚስትሪ ማሻን እና ሌሎችም የህክምና መገልገያ ቁሳቁሶችን ነው የክልሉ ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ በድጋፍ ያገኘው።

የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ ለተደረገው ድጋፍ ምስጋና አቅርቧል።

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Scroll to Top