የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ የጤና እግር ኳስ ቡድን ተጋጣሚውን በማሸነፍ ውድድሩን በድል ጀምሯል።

የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ የጤና እግር ኳስ ቡድን ተጋጣሚውን በማሸነፍ ውድድሩን በድል ጀምሯል።

አርባ ሁለት ቡድኖች በሚሳተፋበት የጤና እግር ኳስ ስፖርት ውድድር ላይ እየተሳተፈ የሚገኘው የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ የጤና እግር ኳስ ቡድን የአብክመ ፕላንና ልማት ቢሮን 4ለ0 በሆነ ውጤት አሸንፏል።

የባሕርዳር ከተማ አስተዳደር ወጣቶችና ስፖርት መምሪያ ከፌዴሬሽኖች ጋር በመተባበር የ2018 ዓ/ም የግልና የመንግስት ተቋማት የጤና ስፖርት ውድድር “ስፖርታዊ እንቅስቃሴ ለቀልጣፋ እና ምቹ አገልግሎት” በሚል መሪ ቃል እየተካሔደ ይገኛል።

በዚህ ውድድር ላይም የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ የጤና እግር ኳስ ቡድን ከአ.ብ.ክ.መ ፕላንና ልማት ቢሮ ጋር ከቀኑ 10:00 ሰዓት በአጼ ቴዎድሮስ ስታዲየም የመጀመሪያ ጨዋታውን አድርጎ ከማራኪ አጨዋወት ጋር 4 ለ 0 በማሸነፍ ጅማሮውን አሳምሯል።

የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ የኮሙኒኬሽን እና ህዝብ ግንኙነት ዋና መምሪያ ኃላፊ ረዳት ኮሚሽነር ክንዱ ወንዴ በውድድር ቦታው ተገኝተው እንደገለጹት የክልሉ ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ የጤና ስፖርት ውድድሮች ጤናን ከመጠበቅ ባለፈ ሠላምን፣ መተሳሰብን እና አንድነትን ለማስፈን ጉልህ ድርሻ ስላላቸው ተቋማችን በዚህ ውድድር ተሳታፊ መሆኑ ጠቀሜታው የጎላ ነው ብለዋል።

ስፖርት ምንጊዜም ቢሆን የወንድማማችነት፣ የሰላም እና የአንድነት ማሳያ መድረክ ነው ያሉት ረዳት ኮሚሽነር ክንዱ ወንዴ ብቁና ተወዳዳሪ የፖሊስ ሰራዊት ለማፍራት ከፍተኛ ሚና እንደሚኖረውም ጠቁመዋል።

የጤና ስፖርት ውድድር ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያለው ሲሆን በዋናነትም ተቋማዊ ፍቅር እንዲፈጠር ፣ በተሳታፊ ተቋማት መካከል የእርስበርስ ግንኙነት እንዲዳብር፣ ሰራተኞች የአካል ብቃት እንቅስቃሴ በማድረግ ንቃተ ህሌናቸውን በማሳደግ ውጤታማ ሰራተኛ እንዲሆኑ ያደርጋቸዋል ብለዋል።

የፖሊስ ተቋምን ወክለው የተጫወቱ የእግር ኳስ የጤና ቡድን አባላት ጨዋታው ተጀምሮ እስኪጠናቀቅ ድረስ ያሳዩት ስፖርታዊ ጨዋነትና ለተጋጣሚ አቻቸው ያሳዩት ፍቅር የተቋማችንን መልካም ገጽታ አጉልቶ የሚያሳይ ተግባር በመሆኑ ተጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል ብለዋል።

የጤና ሰፖርት ውድድሩ ጤናን የሚጠብቅ አዕምሮን የሚያነቃቃ በመሆኑ ከእግር ኳስ በተጨማሪም በመረብ ኳስና በሌሎች የስፖርት አይነቶች ለመወዳደር ተቋሙ ዝግጁ እንደሆነም ኃላፊው ጠቁመዋል።

በተጀመረው ውድድር የጤና ስፖርት በተቋማት ደረጃ በእግር ኳስ 42፣ በመረብ ኳስ 25፣ በቴብል ቴንስ፣ በዳርት፣ በቼይዝ እና መሰል የመወዳደሪያ ዘርፎች በምድብ ተከፋፍለው ጨዋታቸውን እንደሚያካሒዱም መረጃዎች ይጠቁማሉ።

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Scroll to Top