በባህርዳር ከተማ አስተዳደር ፖሊስ ለወንጀል መከላከል ተግባር ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑ ተገለጸ
የማህበረሰብ ዓቀፍ ፖሊስ አገልግሎት ወንጀልን አስቀድሞ የሚያከሽፍ እና ለሚፈጠሩ ችግሮች አካባቢያዊ መፍትሄ የሚሰጥ ማህበረሰብ ማፍራት የተቻለበት አሰራር ነው።
በባህርዳር ከተማ አስተዳደር በሁሉም አካባቢዎች ማህበሰረሰቡን ባለቤት ያደረገ የወንጀል መከላከል ስራ መጠናከሩ ተገልጿል።
የባህር ዳር ከተማ አስተዳደር ፖሊስ መምሪያ አዛዥ ኮማንደር ዋለልኝ ቢምረው ለዝግጅት ክፍላችን እንደተገለጹት በከተማው ውስጥ ሊፈጠሩ የሚችሉ ወንጀሎችን ቀድሞ ለመከላከል እና ለሚፈጠሩ ችግሮችም የፖሊስን መፍትሄ ብቻ የማይጠብቅ ማህበረሰብ መፍጠር የተቻለበት ተግባር ተጠናክሮ መቀጠሉን ተናግረዋል።
ከተሳታፊነት ባለፈ ባለቤት የሆነ ማህበረሰብ የተፈጠረበት እና ከሁሉም የማህበረሰብ ክፍሎች ጋር ውይይት በማድረግ ወደ ስራ የተገባ መሆኑንም የከተማው ፖሊስ አዛዥ አስታውቀዋል።
ፖሊስ ከማህበረሰቡ ጋር ተቀናጅቶ በሚያደርገው የወንጀል መከላከል ስራ በከተማው ይስተዋሉ የነበሩ የጥይት ተኩስ፣ የእገታ እና የዝርፊያ ወንጀሎችን መቀነስ ተችሏል ሲሉ አብራርተዋል።
ለባህርዳር ከተማ ሰላም መረጋገጥ የማህበረሰቡ ድርሻ ጉልህ መሆኑን የገለጹት የፖሊስ አዛዡ በዚህም የነበሩ ክልከላዎች ተነስተዋል ብለዋል።
ማህበረሰብ አሁን ላይ ቀን እና ሌሊት አካባቢውን እየጠበቀ ይገኛል ሲሉ የባህር ዳር ከተማ አስተዳደር ፖሊስ መምሪያ አዛዥ ኮማንደር ዋለልኝ ቢምረው አረጋግጠዋል።
በባህር ዳር ከተማ አስተዳደር ፖሊስ መምሪያ የወንጀል መከላከል ምክትል መምሪያ ኃላፊ ኮማንደር ንብረቱ ሞላ በበኩላቸው የባህርዳር ከተማ ህዝብ ለጸጥታ ኃይሉ መረጃን ከመስጠት ባለፈ አጥፊዎችን የሚመክር፣ ወንጀል ፈጻሚዎችን የሚቆጣጠር እንዲሁም ወንጀልን አስቀድሞ የሚከላከል ነው ብለዋል።
ፖሊስ ከከተማው ነዋሪ ጋር ባለው መልካም ግንኙነት የወንጀል መከላከል ስራን ቀላል አድርጎታል ያሉት ደግሞ በከተማ አስተዳደሩ ፖሊስ መምሪያ የ2ኛ ፖሊስ ጣቢያ አዛዥ ኮማንደር ዘሪሁን አስራደ ናቸው።
ፖሊስ የሚያደርገው የወንጀል መከላከል እና ሰላምን የማረጋገጥ ተግባር ያለ ማህበረሰቡ ድጋፍ እና ተሳትፎ ውጤት አልባ ድካም መሆኑን የ2ኛ ፖሊስ ጣቢያ አዛዥ አክለዋል
በውጤት የታጀበ ለውጥ ለማምጣት ማህበረሰቡን ቀዳሚ ተዋናይ ያደረገ የወንጀል መከላከል ስራ መስራት ሚናው የጎላ መሆኑንም ኮማንደር ዘሪሁን ጠቅሰዋል።
በምሽት አካባቢያቸውን ሲጠብቁ ያገኘናቸው በባህርዳር ከተማ የ08 ቀበሌ ነዋሪው አቶ አለሙ ገሰሰ ከፖሊስ ጋር በመቀናጀት አካባቢያችን ከወንጀል ድርጊት ለመጠበቅ የበኩላችን ድርሻ እየተወጣን እንገኛለን ብለዋል።
በአካባቢያችን ለሚከሰቱ ቀላል ችግሮች አካባቢያዊ መፍትሔ ለመስጠት የሚያስችል አደረጃጀት ተዋቅሮ ወደ ስራ ገብተናል ሲሉ ገልጸዋል።
ሌላዋ የከተማዋ ነዋሪና በማህበረሰብ ዓቀፍ ወንጀል መከላከል አደረጃጀት የገለልተኛ አማካሪ ምክር ቤት አባል ወይዘሮ አወቀች ባዬ በበኩላቸው ወንጀል ፈጻሚዎች የሚወጡት ከማህበረሰቡ የሚጎዳውም ማህበረሰቡን በመሆኑ አካባቢያችን ሰላም ማድረግ ቀዳሚው ተግባራችን ነው ሲሉ ጠቁመዋል።
ማንኛውም ወንጀል ከማህበረሰቡ እይታ ሊሰወር አይችልም የሚሉት ወይዘሮ አወቀች ነዋሪው ከፖሊስ እና ከሌሎች የጸጥታ አካላት ጋር ተቀናጅተው መስራታቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉም አረጋግጠዋል።
ሰላም በእኛ የሚረጋገጥ፣ ለእኛ የሚጠቅም እና ትኩረት የሚሻ የወል ሀብታችን በመሆኑ ከጸጥታ ኃይሉ ጎን በመሆን ሰላማችን እናረጋግጣለን ሲሉም አክለዋል።
















