በህብረተሰብ የሚወደድ እና የሚከበር የፖሊስ ሰራዊት እየተገነባ መሆኑ ተገለጸ።
የአማራ ክልል ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ክብርት ወይዘሮ ፋንቱ ተስፋዬን ጨምሮ የምክር ቤቱ ቋሚ ኮሚቴ አመራር እና አባላት የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ የጀመረውን የዲጅታላይዜሽን ስራ ጎብኝተዋል።
የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ኮሚሽነር ዘላለም መንግስቴ (ዶ/ር) እንደገለጹት በተቋሙ የነበሩ ኋለ ቀር አሰራሮችን ወደ ዘመናዊ የአሰራር ስርዓት በማምጣት ሠራዊቱ በተሠማራበት ሙያ ብቁና ውጤታማ እንዲሆን እየተደረገ ይገኛል ብለዋል።
ህብረተሰቡ በፖሊስ ላይ ያለው እምነት እንዲጨምር ቅንጅታዊ ስራው እንዲዳብር በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የተደገፈ አሰራርን መከተል ይገባል አክለዋል።
“የፖሊስ ሰራዊት በወንጀለኞች የተፈራ ለሰላማ ፈላጊ ህብረተሰብ የሚወደድ እና የሚከበር ሰራዊት መገንባት ቀዳሚው ተግባር በመሆኑ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል”።
የተጀመረው የሪፎርም ስራ ለሠራዊቱ መነሳሳትን የፈጠረ እና በተመደበበት ሙያ በኃላፊነት እንዲሰራ ያደረገ እንደሆነም ኮሚሽነር ዘላለም መንግስቴ (ዶ/ር) ተናግረዋል።
በተቋሙ በተደጋጋሚ በህብረተሰቡ ይነሱ የነበሩ የሰበዓዊ መብት አያያዝ ችግሮችን ለመቅረፍ ዘመናዊ ቴክኖሎጅን በመጠቀም እተሰራ እንደሆነም አብራርተዋል።
ተቋሙ በጀመረው የለውጥ ስራ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የተደገፉ ካሜራዎችን በማስገጠም ውጤታማ የክትትል ስራዎችን በማድረግም ውጤታማ የወንጀል መከላከል ስራ በክልሉ ሁሉም አካባቢዎች እየተሰራ መሆኑንም ገልፀዋል።
አሁን የተጀመረው የለውጥ ስራ በዲጅታላይዜሽን የታገዘ እና የተቀናጀ የመረጃ አያያዝ ስርዓትን በመዘርጋት ጥራቱን የጠበቀ የምርመራ ስራ እየተሰራ እንደሚገኝም አክለዋል።
የሰራዊቱን አቅም የሚያሳድግ እና እንደ ፖሊስ ወጥ የሆነ የአሰራር ስርዓት እንዲፈጠር በትኩረት አየተሰራ መሆኑንም ኮሚሽነር ዘላለም መንግስቴ (ዶ/ር) ጠቁመዋል።
የአማራ ክልል ምክር ቤት ዋና አፈ-ጉባኤ ክብርት ፋንቱ ተስፋዬ ፖሊስ ከመደበኛ ስራው ጎን ለጎን በክልሉ የተከሰተውን ችግር ለመቅረፍ ህይወቱን እየሰጠ ባለበት የተሰራ የለውጥ ስራ መሆኑ ተቋሙ ወደ ቀደመ ክብሩ እየተመለሰ መሆኑን እንደሚያመላክት ገልጸዋል።
የተጀመረው የዲጅታላይዜሽን ስራ በህብረተሰቡ ይስተዋል የነበረውን የመልካም አስተዳደር ቅሬታ የሚፈታ ተግባር እንደሆነም ጠቁመዋል።
በአጭር ጊዜ ውስጥ ዘመናዊ የዲጅታላይዜሽን ስራን መተግበሩ ህዝብን ለማገልገል የገባውን ቃል በተጨባጭ እያሳየ እንደሚገኝም ክብርት ፋንቱ ተስፋዬ ገልጸዋል።
ቀደም ሲል ማህበረሰቡ ተቋሙን ይፈሩት እንደነበር ገልጸው አሁን ላይ ለፖሊስ ተቋም በሚሰጠው አገልግሎት ክብር እንዲኖረው ያደረገ መሆኑን አብራርተዋል።
የጉብኝቱ ተካፋይ የምክር ቤት አባላት በበኩላቸው ፖሊስ በአጭር ጌዜ ዉስጥ ተስፋ ሰጭ የሪፎርም ስራ ያከናወነ መሆኑን ገልፀዉ ፣ የጀመረው የለውጥ ስራ እዉቀተ ላይ የተመሰረተ ፣ እና በቴክኖሎጂ የሚጠቀም ሰራዊት እየተፈጠረ እንደሆነም ገልጸዋል።
ፖሊስ የጀመረው የዲጅታላይዜሽን ስራ ከህብረተሰቡ ጋር ያለውን ግንኙነት የሚያጠናክር ዘመናዊ አሰራርን የሚያጎለብት በመሆኑ እስከታች ድረስ ተግባራዊ መደረግ እንደሚገባም የጉብኝቱ ተሳታፊዎች አስታውቀዋል።
ፖሊስ የጀመረውን የዲጅታላይዜሽን ስራ ለማስቀጠል እና ከህብረተሰቡ ጋር ያለውን ግንኙነት ለማጠናከር የሚጠበቅባቸውን ድጋፍ እና ክትትል እንደሚያደርጉም የጉብኝቱ ተሳታፊ የምክር ቤት አባላት ገልጸዋል።

























