“ፖሊስ የሚያከናውነው የምርመራ ስራ የፍትህ ሂደቱ መሰረት ነው!” ኮሚሽነር ዘላለም መንግሥቴ (ዶ/ር)
በአማራ ክልል የሙስና ወንጀል ክስ አመሰራረትና የቅንጅት ስራ ላይ ያተኮረ የምክክር መድረክ ተካሄደ
በአማራ ክልል የሙስና ወንጀሎችን በብቃት ለመከላከል እና የሕግ ተጠያቂነትን ለማረጋገጥ እንዲሁም የሕዝብን ሀብት እና የክልሉን በጀት ከምዝበራ ለመታደግ የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ እና የፍትህ ቢሮ በሙስና ወንጀሎች የክስ አመሰራረት እና የቅንጅት ስራ ላይ ያተኮረ ከፍተኛ የምክክር መድረክ አካሂደዋል።
መድረኩ በተለይም በሙስና መዝገቦች ላይ የሚታዩ የክስ አመሰራረት ክፍተቶችን ለመሙላት እና የፍትህ ሂደቱን ለማፋጠን እንዲሁም በክልሉ እየተስተዋሉ ያሉ የሙስና ወንጀሎችን በሕግ ጥላ ስር ለማዋልና የክስ አመሰራረት ሂደቱን በሳይንሳዊ ማስረጃ ለመምራት የሚያስችል እንደሆነ በመድረኩ ተመላክቷል።
እስካሁን ባለው ሂደት የታዩ የአሰራር መጓተቶች እና በቅንጅት ማነስ ምክንያት የሚስተጓጎሉ የሙስና መዝገቦች ላይ በሁለቱ ተቋም አመራሮች ጥልቅ ትንታኔ ቀርቧል።
በመድረኩ ላይ የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ እና የአማራ ክልል ፍትህ ቢሮ ኃላፊ ተገኝተው ተቋማዊ ቅንጅትን የሚያጠናክሩ ንግግሮችን አድርገዋል።
ኮሚሽነር ዘላለም መንግሥቴ (ዶ/ር) የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ “ፖሊስ የሚያከናውነው የምርመራ ስራ የፍትህ ሂደቱ መሰረት ነው” ሲሉ ገልጸዋል።
እንደ ኮሚሽነር ዘላለም መንግሥቴ (ዶ/ር) ገለጻ በምርመራ ወቅት የሚሰበሰቡ የሰውና የሰነድ ማስረጃዎች ለዓቃቤ ሕግ ክስ መመስረት በቂና አሳማኝ መሆን አለባቸው።
ሙስና ሀገርን እና ክልሉን የሚያደቅ የወንጀል ድርጊት መሆኑን ያዝገነዘቡት ኮሚሽነር ዘላለም መንግሥቴ (ዶ/ር) በምርመራ እና በክስ ሂደት ላይ ቸልተኝነት በሚያሳዩ ባለሙያዎች ላይ ጥብቅ ቁጥጥር ማድረግ እንደሚገባም አስታውቀዋል።
በተቋማቶቻችን መካከል ያለው ቅንጅት ሲላላ ወንጀለኞች ዕድል ያገኛሉ ያሉት ኮሚሽነር ዘላለም መንግሥቴ (ዶ/ር) ይህንን ክፍተት ለመድፈን ፖሊስ የምርመራ ጥራቱን ለማሳደግ ቁርጠኛ ነው ሲሉ አሳስበዋል።
ፖሊስ የሚያከናውነው የምርመራ ስራ ጥራት ለዓቃቤ ሕግ የክስ ጥንካሬ መሰረት ነው ያሉት ኮሚሽነር ዘላለም መንግሥቴ (ዶ/ር) የምርመራ መዝገቦቻችን በሳይንሳዊ ማስረጃና በቴክኖሎጂ ተደግፈው ካልተገነቡ የፍትህ መዛባትን ያስከትላሉ ብለዋል።
የሙስና ወንጀል ምርመራዎች ሳይንዛዙና መረጃ ሳይጠፋ በወቅቱ ተጠናቀው ለፍርድ ቤት እንዲቀርቡ ማድረግ ይገባል ብለዋል።
በሁለቱ ተቋማት መካከል የሚደረጉ የደብዳቤ ልውውጦች እና የሰነድ ዝውውሮች በቴክኖሎጂ የታገዙ እንዲሆኑ በማድረግ፣ መረጃ የመጥፋት ወይም የመለወጥ እድልን ለማጥበብ እንደሚሰራ ኮሚሽነር ዘላለም መንግሥቴ (ዶ/ር) ተናግረዋል።
በሁለቱ ተቋማት መካከል ያለው የመረጃ ልውውጥ ፈጣን እና ግልጽ መሆን እንዳለበት ያስታወቁት ኮሚሽነር ዘላለም መንግሥቴ (ዶ/ር) ይህም ለወንጀለኞች ክፍተት እንዳይፈጥር የሚያስችል መሆኑን አክለው ገልጸዋል።
አቶ ብርሃኑ ጎሹም የአማራ ክልል ፍትህ ቢሮ ኃላፊ በበኩላቸው “የሙስና ወንጀል ውስብስብ ባህሪ ያለው በመሆኑ፣ ዓቃቤ ሕግ እና ፖሊስ ከመጀመሪያው የምርመራ ምዕራፍ ጀምሮ በቅንጅት መስራት ይኖርባቸዋል ብለዋል።
በሙስና ወንጀል ምርመራ ወቅት የሚሰበሰቡ ማስረጃዎች ጥራት እና ለክስ ያላቸው ዝግጁነት ላይ በቂ ውይይት ሊደረግባቸው እንደሚገባም አቶ ብርሃኑ ጎሹም ጠቁመዋል።
የክስ አመሰራረት ሂደታችን በጥራት ላይ የተመሰረተ ካልሆነ የሕዝብን ሀብት የበሉ ግለሰቦች በሕግ ክፍተት እንዲያመልጡ በር ይከፍታል ሲሉ አክለው አብራርተዋል።
የፍትህ ቢሮው የሕግ ክፍተቶችን የሚደፍን ጥራት ያለው ክስ ለመመስረት ቁርጠኛ መሆኑንም አጽንኦት ሰጥተው አብራርተዋል።
የሙስና ወንጀል ውስብስብና ማስረጃን የማጥፋት ባህሪ ያለው በመሆኑ የገለጹት የፍትህ ቢሮ ኃላፊው ከእንግዲህ በማስረጃ ጥራት ጉድለት የሚወድቅ የሙስና መዝገብ ሊኖር አይገባም! ሲሉ አስጠንቅቀዋል።
የውይይቱ ተሳታፊዎች በበኩላቸው በማስረጃ እጥረት ወይም በአሰራር ግድፈት ምክንያት የሚቋረጡ የሙስና ክሶችን ቁጥር በከፍተኛ ደረጃ መቀነስ ይጠበቃል ብለዋል።
የሙስና ወንጀል ምርመራ እና የክስ ሂደት ጊዜን በመቆጠብ የህዝብን የፍትህ ጥያቄ መመለስ ጊዜ የማይሰጠው ጉዳይ መሆኑ አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል።
ጠንካራ የሕግ ተጠያቂነት መኖሩ ሌሎች ተመሳሳይ የሙስና ድርጊቶችን እንዳይፈጽሙ የማስጠንቀቂያ ደወል ይሆናል ሲሉም ተወያዮች አረጋግጠዋል።
ይህ የውይይት መድረክ በክልሉ የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን ለመመለስና የህዝብን ሀብት ከምዝበራ ለመከላከል የሚደረገው ጥረት አካል መሆኑ ተመልክቷል።
በምርመራ እና በክስ ሂደት ላይ የሚሳተፉ መሪዎች እና ባለሙያዎች ከሙስና የጸዱ እንዲሆኑ እና በማንኛውም መዘግየት ወይም ክፍተት ላይ ተጠያቂነት እንዲሰፍን የሚያስችል አሰራር ሊኖር እንደሚገባም ተጠቁሟል።
የሙስና ወንጀልን ለማረጋገጥ የፎረንሲክና የኦዲት ግኝቶችን በአግባቡ የመጠቀም አስፈላጊነትንም ተሳታፊዎች አንስተዋል።
በመጨረሻም “የሕግ የበላይነት ተረጋግጦ የክልሉ ልማት ይፋጠናል!” ሲሉ ተወያዮች አረጋግጠዋል።
















