የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ በኢትዮጵያ ፖሊስ ታሪክ የመጀመሪያ የሆነውን ልዩ ኮማንዶ አስመረቀ

የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ በኢትዮጵያ ፖሊስ ታሪክ የመጀመሪያ የሆነውን ልዩ ኮማንዶ አስመረቀ

‎የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ በክቡር ኮሚሽነር ጀነራል ሀሳብ አፍላቂነት በኢትዮጵያ ፖሊስ ታሪክ የመጀመሪያ የሆነውንና ለረዥም ጊዜ ሥልጠና የወሰደ ልዩ ኮማንዶ የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ክቡር ተመስገን ጥሩነህ እና ክቡር የአፋር ክልል ፕሬዚዳንት አወል አርባ በተገኙበት በኢትዮጵያ ፖሊስ አካዳሚ በታላቅ ድምቀት አስመርቋል።

የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ክቡር ተመስገን ጥሩነህ በምረቃ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ በሰጡት የሥራ መመሪያ ለሕገ- መንግስታዊ ሥርዓት ዋስትና እና ጠበቃ የሆነ፣ በሙያው የሚኮራ፣ ሕጎችን በአግባቡ በመተግበር የሕዝብ ፍቅርና አመኔታ ያለው ጠንካራ ፕሮፌሽናልና በቴክኖሎጂ የተደገፈ የፖሊስ ተቋም እየተገነባ ይገኛል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ የሪፎርም አካል የሆነ ልዩ ኮማንዶ ለመጀመሪያ ጊዜ በራስ አቅም በማሰልጠን ማስመረቅ መቻሉ የሀገራችንን ሰላምና ደህንነት በማረጋገጥ ወንጀልን በመከላከልና የምንመኘውን የሀገራችንን ዕድገት ዕውን ለማድረግና ለማሳለጥ ከፍተኛ ሚና እንዳለውም ተናግረዋል።

የፖሊስ ኃይላችን ከሀገራችን ዕድገት ጋር የተጣጣመ ፤የኢትዮጵያን ከፍታ የሚመጥን እንዲሆን መንግስት አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍ እንደሚያደርግም ክቡር ምክትል ጠቅላይ ሚንስትር ጨምረው ገልጸዋል።

ክቡር የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል በበኩላቸው ስልጠናው ማንኛውንም ልዩ ኦፕሬሽኖች እና ግዳጆችን በከፍተኛ ብቃት መፈፀም የሚያስችል ጠንካራ አቅም መፍጠሩን ገልፀዋል።

ይህም ባለፉት ዓመታት የሠራነው የሪፎርም ውጤት አንዱ ማሳያ ነው ያሉት ክቡር ኮሚሽነር ጀነራል በሪፎርሙ በሕግ እና በአሠራር፣ በሰው ኃይል፣ በቴክኖሎጂ እና በሎጂስቲክስ፣ በውስጥና በውጪ ግንኙነት በሁሉም መስክ በሰራነው ስኬታማ ሪፎርም የሀገር አለኝታ የሆነ፤ ገለልተኛና ሙያዊ ብቃት ያለውና በማድረግ አቅሙም ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ የሆነ የፖሊስ ተቋም መገንባት ችለናል ማለታቸውን የፌደራል ፖሊስ አስታውቋል።

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Scroll to Top