ለታጣቂ ቡድኑ ሊደርስ የነበር የጦር መሳሪያ በጸጥታ ኃይሎች ቁጥጥር ስር ዋለ

ለታጣቂ ቡድኑ ሊደርስ የነበር የጦር መሳሪያ በጸጥታ ኃይሎች ቁጥጥር ስር ዋለ

መነሻውን ባህርዳር አድርጎ ወደ ሰሜን ወሎ በመጓጓዝ ላይ የነበረ የጦር መሳሪያ በደብረታቦር ከተማ አስተዳደር የጸጥታ ኃይሎች የተቀናጀ ስራ መያዙን የከተማ አስተዳደሩ ፖሊስ መምሪያ አስታውቋል፡፡

በመምሪያው የወንጀል ምርመራ ምክትል መምሪያ አዛዥ ኮማንደር መሳፍንት አባይ እንደተናገሩት ከብሄራዊ መረጃ አገልግሎት ጋር በቅንጅት በተሰራ ስራ ለታጣቂ ቡድኑ ሊደርስ የነበር የጦር መሳሪያ ነው በቁጥጥር ስር የዋለ ብለዋል።

እንደ ኮማንደር መሳፍንት ገለጻ መነሻውን ባህርዳር አድርጎ ከመደበኛ መንገድ ውጭ ከሀሙሲት በማህደረ ማርያም ወደ ሰሜን ወሎ ሲጓዝ የነበረ ታርጋ ቁጥር ኮድ 3 አማ 17638 በሆነ አነስተኛ ተሽከርካሪ ላይ የነበረ አንድ ብሬን እና አንድ ስናይፐር የጦር መሳሪያ ከሁለት ተጠርጣሪዎች ጋር በደብረታቦር ከተማ አባረጋይ በተባለው የኬላ ፍተሻ በቁጥጥር ስር መዋሉን ነው ያብራሩት፡፡

የውስጥ እና የውጭ ጠላቶች በመተባበር የሚፈጽሙት ሀገርን የማተራመስ እና የህዝብን ሰላም የማናጋት ተግባር በብሄራዊ መረጃና ደኅንነት እንዲሁም በከተማ አስተዳደሩ የጸጥታ መዋቅር የተቀናጀ ስራ የጥፋት ተልዕኳቸውን በተከታታይ ማክሸፍ መቻሉንም አንስተዋል።

ህገ-ወጥ ድርጊት ትልቅ ጉዳት ያለው መሆኑን ያነሱት ኮማንደር መሳፍንት አባይ ድርጊቱን ለመከላከል አጎራባች ወረዳዎች እና ዞኖች ተቀናጅተው ሊሰሩ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

ማህበረሰቡ ህገወጥ ድርጊትን ለማስቆም ከጸጥታ ኃይሉ ጋር ተባብሮ ሊሰራ እንደሚገባም ኮማንደር መሳፍንት አባይ የደብረታቦር ከተማ አስተዳደር ፖሊስ መምሪያ የወንጀል ምርመራ ምክትል መምሪያ አዛዥ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Scroll to Top