“የፖሊስ ተቋምን ለማሳደግ ሙያውን የሚወድ እና በአላማው የጸና ሰራዊት መገንባት ይገባል!” ኮሚሽነር ዘላለም መንግስቴ (ዶ/ር)

“የፖሊስ ተቋምን ለማሳደግ ሙያውን የሚወድ እና በአላማው የጸና ሰራዊት መገንባት ይገባል!” ኮሚሽነር ዘላለም መንግስቴ (ዶ/ር)

በአማራ ክልል ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ሲሰጥ የቆየው የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ የጎጃም ቀጣና ፖሊስ አመራሮች እና አባላት የጂኦ ስትራቴጂክ እና የአመራር አቅም ግንባታ ስልጠና ተጠናቋል፡፡

በስልጠናው ለተሳተፉ የፖሊስ አመራሮች እና አባላት በቪዲዮ ኮንፈረስ የማጠቃለያ ሀሳብ እና የስራ መመሪያ የሰጡት ኮሚሽነር ዘላለም መንግስቴ (ዶ/ር) የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ በአዕምሮው የዳበረ በአካሉ የጎለበተ የፖሊስ ሰራዊት ለመፍጠር የተሰጠ ስልጠና መሰረታዊ ለውጥን ያመጣል ብለዋል።

እንደ ኮሚሽነር ዘላለም መንግስቴ (ዶ/ር ) ገለጻ የፖሊስ ተቋምን ለማሳደግ በየትኛውም ደረጃ የሚገኝ “የፖሊስ አባል ሙያውን ሊወደው እና ለቆመለት አላማ ሊጸና ይገባል” ብለዋል።

ስልጠናው የፖሊስን አገልግሎት አሰጣጥ በጥራት፣ በፍጥነት እና በስፋት ለህዝብ ለማድረስ የሚያስችል መሆኑንም አብራርተዋል።

ተቋማዊ ተልዕኮዎችን ተረድቶ የመፈጸም አቅሙን በማሳደግ በታማኝነት እና በኃላፊነት የሚሰራ የፖሊስ ሰራዊት እንዲሆን የሚያስችል ስልጠና መሆኑንም ኮሚሽነር ዘላለም መንግስቴ (ዶ/ር ) ጠቁመዋል።

የአማራ ክልል ፖሊስ የህዝብን ሰላም እና ደኅንነት ለማስከበር የህይወት እና የአካል መስዋዕትነት እየከፈለ ይገኛል ሲሉ አብራርተዋል።

የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ የጀመረውን የለውጥ ስራ በኃላፊነት ተሸክሞ የሚያራምድ የፖሊስ ሰራዊት እየተገነባ እንደሆነም ኮሚሽነር ዘላለም መንግስቴ (ዶ/ር) አስታውቀዋ።

የተሰጠውን የአቅም ግንባታ ስልጠና ተግባራዊ በማድረግ የክልሉን ፖሊስ ወደ ቀደመ ክብሩ እና ዝናው መመለስ ይጠበቅብናል ሲሉ አክለዋል።

የአማራ ክልል ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ፕሬዝዳንት ምክትል ኮሚሽነር አበበ ደለለ በበኩላቸው ስልጠናው የፖሊስ መሪዎች እና አባላት እንደ ክልል እና እንደ ሀገር ያለውን ተጨባጭ ሁኔታ ባገናዘበ መልኩ ለቀጣይ ተልዕኮ ዝግጁ ለመኾን የሚያስችል መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ማኅበረሰቡን ያላቀፈ የወንጀል መከላከል ስራ ውጤታማ ሊሆን አይችልም ያሉት ምክትል ኮሚሽነር አበበ ደለለ ኅብረተሰቡን ባሳተፈ መልኩ እና በመረጃ የተደገፈ ተግባርን መከወን ይጠበቃል ሲሉ አክለው ተናግረዋል፡፡

የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ የሰው ኃይል ልማትና አስተዳደር ዋና መምሪያ ኃላፊ ረዳት ኮሚሽነር አብዮት ሽፈራው ስልጠናው የፖሊስን አቅም በማሳደግ የከፍታ ዘመን ማሳያ እና ዘመናዊ አሰራርን የተከተለ የፖሊስ ሰራዊት ለመገንባት ያስችላል ብለዋል።

የሰው ኃይል አስተዳደር እና ልማት ስራችን በማዘመን የመልካም አስተዳደር ችግሮችን መቅረፍ ይጠበቅብናል ያሉት ረዳት ኮሚሽነር አብዮት ሽፈራው የህግ ማስከበር ስራችን በማጠናከር የክልሉን ህዝብ ሰላምና ደኅንነት ማስጠበቅ ከሁሉም የፖሊስ አመራርና አባላት እንደሚጠበቅም አሳስበዋል፡፡

የምሥራቅ ጎጃም ዞን ፖሊስ መምሪያ አዛዥ ኮማንደር ግርማ ጫኔ በተቋማዊ የለውጥ ስራዎች የተገኙ ውጤቶች እና በቀጣይ ሊያጋጥሙ የሚችሉ ፈተናዎችን ለመለየት አቅም የፈጠረ ስልጠና ስለመሆኑን ገልጸዋል።

ኅብረተሰቡ ካጋጠመው ግጭት ተላቆ ሰላማዊ ኑሮውን እንዲቀጥል ለማስቻል በቅንጅት መሥራት እንደሚገባ የጋራ መግባባት ላይ የተደረሰበት ስልጠና መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

የስልጠናው ተሳታፊዎች ሙያው የሚጠይቀውን ስነ-ምግባር በመላበስ ኅብረተሰቡን አቅፎ መስራት ከተቻለ ውጤት ማምጣት እንደሚቻል ያሳየ እና መነሳሳትን የፈጠረ ስልጠና መውሰዳቸውን ገልጸዋል፡፡

የክልሉን ሰላም ለማማረጋገጥ ከህብረተሰቡ ጋር ያለውን ቅንጅታዊ አሰራር አጠናክረው እንደሚቀጥሉም አረጋግጠዋል፡፡

ስልጠናው በቀጣይም እስከታች ተደራሽ የሚደረግ ሲሆን ሁሉም የተጣለበትን ሙያዊ ኃላፊነት ተረድቶ እንዲሰራ የፖሊስ ሰራዊቱን ተከታታይነት ያለው የአቅም ግንባታ ስልጠና መስጠት እንደሚገባ ተጠቁሟል።

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Scroll to Top