የአማራ እና የአፋር ክልል ተጎራባች ዞኖች የሰላም ግንባታ እና የግጭት አፈታት የምክክር መድረክ ተካሄደ።
የአማራ እና የአፋር ክልል ተጎራባች ዞኖች እና ወረዳዎች የተውጣጡ የጸጥታ አመራሮች እና ባለሙያዎች የተሳተፉበት በሰላም ግንባታ እና በግጭት አፈታት ላይ ያተኮረ የምክክር መድረክ በሰላም ሚኒስቴር እና በUNDP ድጋፍ ነው በኮምቦልቻ ከተማ የተሰጠው።
በመድረኩ ላይ የሰላም ሚኒስቴር ሚኒስትር ድኤታ አቶ ቸሩጌታ ገነነ፣ ሌተናል ጀነራል አሰፋ ቸኮል የምስራቅ እዝ አዛዥ፣ ኮሚሽነር ዘላለም መንግስቴ (ዶ/ር) የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ፣ እሸቱ የሱፍ (ዶ/ር) የአማራ ክልል ሰላም እና ጸጥታ ቢሮ ኃላፊ፣ አቶ አስቻለ አላምሬ የአማራ ክልል ሚሊሻ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ እንዲሁም የአፋር ክልል ሰላምና ጸጥታ ቢሮ ኃላፊ፣ የአፋር ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር እና የሁለቱ ክልሎች አጎራባች የዞን እና የወረዳ አመራሮች ተገኝተዋል።
ይህ ምክክር በሁለቱ ክልሎች መካከል ዘላቂ ሰላምን ለማጠናከር እና ሊከሰቱ የሚችሉ ግጭቶችን በዘላቂነት ለመፍታት የሚያስችሉ እውቀቶችንና ክህሎቶችን ለማስጨበጥ ያለመ መሆኑ በመድረኩ ከቀረበው ሰነድ ለማወቅ ተችሏል።
በቀረበው ሰነድ ላይ ሰፊ ውይይት በማድረግ በቀጠናው የሚንቀሳቀሱ ጽንፈኞችን፣ ፀረ-ሰላም እና የሽብር ኃይሎችን በቅንጅት በመሰራት የአካባቢውን ደኅንነት ማረጋገጥ እንደሚገባም ተገልጿል።
ልዩ ልዩ አደረጃጀቶችን በመጠቀም እና የግንኙነት ስርዓት በመዘርጋት የሁለቱን ህዝቦች የቆየ ወዳጅነት ማጠናከር እንደሚያስፈልግ የጋራ መግባባት ላይ መደረሱን ከስፍራው የደረሰን መረጃ ያመለክታል።
ኮሚሽነር ዘላለም መንግስቴ (ዶ/ር) የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ስልጠናው በሁለቱ ክልሎች አጎራባች አካባቢዎች ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን የጸጥታ አመራሮች እና አባላት የበኩላቸውን አስተዋፅኦ እንዲያበረክቱ ያስችላቸዋል ብለዋል።
የሁለቱ ክልሎች የስራ ኃላፊዎቹ በውይይት መድረኩ ላይ በመገኘት አጎራባች አካባቢዎች ለሚከሰቱ ግጭቶች አንኳር የሆኑ ምክንያቶችን በመለየት እንደ ሽምግልና እና ድርድር ያሉ ዘላቂ የግጭት መፍቻ መንገዶችን እንዲጠቀሙ የሚያስችል መሆኑንም አስታውቀዋል።
ከጸጥታ ስራ ባሻገር የማህበረሰብ ተሳትፎን ያካተተ ሰላምን የማስፈን ስልቶችን በመቅረጽ በሁለቱ ክልሎች የጸጥታ አካላት መካከል ያለውን ቅንጅትና መረጃ ልውውጥ ለማጠናከር የሚያስችል መሆኑን ነው የገለጹት።
ይህ አይነቱ የጋራ ውይይት በክልሎች መካከል መግባባትን እና እምነትን በመገንባት፣ ዘላቂ ሰላምና ልማትን ለማረጋገጥ ወሳኝ እርምጃ መሆኑን የተሳተፉ አመራሮች እና ባለሙያዎች ገልጸዋል።



