በመንግስት የተደረሰውን የሰላም ስምምነት መሠረት በማድረግ በርካታ ታጣቂዎች እጅ እየሰጡ እንደሆነ ተገለፀ።
በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት እና በአማራ ፋኖ ሕዝባዊ ድርጅት( አፋሕድ) መካከል የተደረገውን የሰላም ስምምነት ተከትሎ በማዕከላዊ ጎንደር ዞን በወገራ ወረዳና ኪንፋዝ ወረዳ አዋሳኝ ቀበሌዎች ሲንቀሳቀሱ የነበሩ 41 ታጣቂዎች የሰላም ስምምነቱን መሰረት በማድረግ ገብተዋል።
በወገራ ወረዳ አምባ ጊወርጊስ ከተማ የገቡ ታጣቂዎችን የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አወቀ አስፈሬ እና የዞኑ ፓሊስ መምርያ አዛዥ ኮማንደር ደሳለኝ አበራ በቦታው ተገኝተው አቀባበል አድርገዋል።
በአቀባበሉ ላይ ንግግር ያደረጉት አቶ አወቀ አስፈሬ እንደገለፁት ከጦርነት ምንም ማትረፍ እንደማይቻል ተረድታቹህና የክልሉን መንግስት የሰላም ስምምነት መሰረት በማድረግ መምጣታቹህ ለአካባቢያቹህ ሰላምና ልማት ያላቹህን ተነሳሽነት የሚያመላክት ነው ብለዋል።
የቡድኑ መሪ ሻለቃ አበበ እንደተናገረው የተፈረመው የሰላም ስምምነት ጥያቄያችን የሚመልስና ለክልልችን ህዝብ እፎይታን የሚሰጥ ነው ብሏል ።
በመንግስት የተደረሰውን የሰላም ስምምነት ተረድተንና ተቀብለን በሰላም መግባት ችለናል ያሉት ደግሞ የቀድሞ ታጣቂዎች ናቸው።
በቀጣይ የቀሩ ወንድሞቻችን የእኛን ፈለግ እንዲከተሉ በማድረግ ለአካባቢያችን ሰላምና እድገት የበኩላችን ለመወጣት ዝግጁ ነን ብለዋል።
ታጣቂወቹ 28 ክላሽ ፣ 4 አብራራው ፣ ሶስት 10 ጎራሸ እና 1 M14 የጦር መሳሪያ ከእነ ሙሉ ትጥቁ ለመንግስት አስረክበዋል።
በፕሮግራሙ የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ አወቀ አስፈሬ እና የዞኑ ፓሊስ መምርያ አዛዥ ኮማንደር ደሳለኝ አበራ ጨምሮ የወረዳው አመራሮችና የመከላከያ ሰራዊት አመራሮች ተገኝተዋል።








