ፖሊስ በሴቶች ላይ የሚደርሰውን ጾታዊ ጥቃት ለመከላከል የህብረተሰብ ግንዛቤ ላይ ትኩረት ማድረግ ይኖርበታል ተባለ።

ፖሊስ በሴቶች ላይ የሚደርሰውን ጾታዊ ጥቃት ለመከላከል የህብረተሰብ ግንዛቤ ላይ ትኩረት ማድረግ ይኖርበታል ተባለ።

የነጭ ሪቫን ቀን በዓል በዓልም አቀፍ ደረጃ ለ34ኛ ጊዜ በሀገራችን ለ20ኛ ጊዜ ‘ጥቃትን የማይታገስ ማህበረሰብ ለትውልድ ግንባታ’ በሚል መሪ ቃል የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ አመራርና አባላት ውይይት አድርጓል።

የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ ምክትል ኮሚሽነርና የአስተዳደር እና ልማት ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ረዳት ኮሚሽነር አያልነህ ተስፋዬ እንደገለጹት በሴቶች ላይ የሚደርሰው ጾታዊ ጥቃት ማህበራዊ ህይወትን የሚያዛባ፤ የሴቶችን ስነልቦና የሚጎዳ ተግባር ነው።

የሴቶችን ሁለንተዊ ተሳትፎ በማሳደግ ራሳቸውን ከሚደርስባቸው ጥቃት ለመከላከል በአካልና በስነልቦና ብቁ እንዲሆኑ የፖሊስ ድጋፍ ጉልህ ድርሻ እንዳለውም ምክትል ኮሚሽነሩ አክለው ተናግረዋል።

ፖሊስ ሴቶች በጾታቸው ምክንያት የሚደርስባቸውን ጥቃት ከመከላከል ባሻገር በኢኮኖሚ እና በማህበራዊ እንቅስቃሴ ያላቸውን ተሳትፎ እንዲያሳድጉ በባለቤትነት መስራት ይኖርበታል ያሉት ምክትል ኮሚሽነሩ እንደ ፖሊስ በየትኛውም ሁኔታ የሴት ልጅ ጥቃትን ዝም ብሎ ማለፍ እንደማይገባም አብራርተዋል።

ፖሊስ የክልሉን ብሎም የሀገርን ሰላም ለማጽናት ከማህበረሰቡ ጋር በመቀናጀት ውጤታማ ስራ እየሰራ መሆኑን የጠቆሙት ምክትል ኮሚሽነሩ በየደረጃው የሚገኙ የፖሊስ አመራርና አባላት ለሴቶች ያላቸውን ክብር እና አጋርነት አጠናክረው መቀጠል ይገባል ብለዋል።

ዋና ኢንስፔክተር ትግዕስት አለምነህ የሴቶችና ህጻናት ድጋፍና ክትትል ባለሙያ በበኩላቸው በዓሉ ሲከበር ወንዶች ነጭ ሪባን ደረታቸው ላይ በማድረግ የሴቶችን ጥቃት በመከላከል ሂደት ውስጥ አጋርነታቸውን የሚገልጹበት፤ በሴቶች ላይ ጥቃት ላለማድረስ እና ጥቃት ሲፈጸምባቸም ዳር ቆሞ ላለማየት ቃል የሚገቡበት ነው ብለዋል፡፡

እንደ ዋና ኢንስፔክተር ትዕግስት ገለጻ ፖሊስ በሴቶች ላይ የሚፈፀሙ ፆታዊ ጥቃቶችን ለመከላከልና ለማስቆም ዓለም እና በሀገር አቀፍ ደረጃ የሚወጡ ሕጎችና ደንቦችን ተረድቶ በመስራት ጥቃት እንዳይፈፀም የቅድመ መከላከል ስራ መስራት ይጠበቅበታል ብለዋል።

በሴቶች ላይ ጥቃት የሚፈፅሙ አጥፊዎችን ለመከላከልና ለሕግ አቅርቦ ተጠያቂ ለማድረግ የሁሉም ዜጋ ኃላፊነት በመሆኑ ተቀናጅቶ መስራት እንደሚገባም ዋና ኢንስፔክተር ትዕግስት ጠቁመዋል።

የውይይቱ ተሳታፊዎች በበኩላቸው ጥቃቱን ለመከላከል የሕብረተሰቡ ተሳትፎ የጎላ መሆኑን በመረዳት እንደ ፖሊስ ማህበረሰብን ማዕከል ያደረገ የመከላከል ሥራ ለመሥራት የጋራ ግንዛቤ ያገኘንበት ነው ብለዋል።

የሴቶች ጥቃትን ለማስቆም በህብረተሰቡ ላይ የሚታዩ የተዛቡ የሥርዓተ ጾታ አመለካከቶችን ማስተካከልና ግንዛቤን ማሳደግ ከፖሊስ እንደሚጠበቅም ተሳታፊዎቹ ጠቁመዋል፡፡

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Scroll to Top