“ፖሊስ አለም አቀፋዊ፣ አሀጉራዊ እና ሀገራዊ የጸጥታ ሁኔታን ተገንዝቦ የተሻለ የፖሊስ አሰራር በመዘርጋት የዜጎችን ሰላም እና ደኅንነት ማረጋገጥ ይገባዋል!” ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ/ር)

“ፖሊስ አለም አቀፋዊ፣ አሀጉራዊ እና ሀገራዊ የጸጥታ ሁኔታን ተገንዝቦ የተሻለ የፖሊስ አሰራር በመዘርጋት የዜጎችን ሰላም እና ደኅንነት ማረጋገጥ ይገባዋል!” ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ/ር)

በአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ ለጎጃም ቀጠና ፖሊሰ አመራሮች እና አባላት የጅኦ ስትራቴጂክ እና የአቅም ግንባታ ስልጠና በአማራ ክልል ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ መሰጠት ተጀምሯል።

በስልጠናው መክፈቻ ስነ-ስርዓት ላይ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር አብዱ ሁሴንን ጨምሮ አማኑኤል ፈረደ (ዶ/ር) በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የአስተዳደር ጉዳዮች ክላስተር አስተባባሪ፣ አቶ ተሾመ ዋለ የደብረ ማርቆስ ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ፣ አቶ ኑርልኝ ብርሃኑ የምስራቅ ጎጃም ዞን አስተዳዳሪ እንዲሁም የ አማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ ስትራቴጂክ እና ከፍተኛ አመራሮች ተገኝተዋል።

የአማራ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ/ር) “ፖሊስ አለም አቀፋዊ፣ አሀጉራዊ እና ሀገራዊ የጸጥታ ሁኔታን ተገንዝቦ የተሻለ የፖሊስ አሰራር በመዘርጋት የዜጎችን ሰላም እና ደኅንነት ማረጋገጥ ይገባዋል!” ሲሉ በዕለቱ ተገኝተው ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር አስገንዝበዋል።

በአሁኑ ስዓት ፖሊስ ወደ ቀደመ ክብሩ እየተመለሰ ያለ እና አዳዲስ ተቋማዊ ስራዎችን እየከወነ በመሆኑ ለፖሊስ ሰራዊቱ አቅሙን የሚያጎለብት እና ሀገራዊ ሁኔታውን ያገናዘበ ስልጠና መሰጠቱ አስፈላጊ መሆኑን ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ/ር) አብራርተዋል።

ህዝብን ከህገ-ወጥ ቡድኖች እና ከታሪካዊ ጠላቶች በጀግንነት በመጠበቅ አኩሪ ድል ማስመዝገብ ይጠበቅባችኋል በማለት ነው ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ/ር) ያሳሰቡት።

የደብረ ማርቆስ ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ተሾመ ዋለ የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት በማስተላለፍ ስልጠናው ያለምንም የጸጥታ ችግር እንዲሰጥ አስፈላጊው የጸጥታ ስራ ተከናውኗል ብለዋል፡፡

የደብረማርቆስ ከተማ ፍጹም ሰላም መሆኗን ያስታወቁት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ተሾመ ዋለ ስልጠናችሁ በስኬት እንዲጠናቀቅ የከተማ አስተዳደሩ አስፈላጊውን ድጋፍ ያደርጋል ሲሉ ተናግረዋል።

ምክትል ኮሚሽነር አበበ ደለለ የአማራ ክልል ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ፕሬዝዳንት እና የስልጠናው አስተባባሪ በአማራ ክልል ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ከሚሰጡ መደበኛ ስልጠናዎች በተጨማሪ አጫጭር የቅም ግንባታ ስልጠና ፕሮግራሞችን በማዘጋጀት የተጀመረውን የፖሊስ የለውጥ መንገድ ከስኬት ለማድረስ በትጋት እየሰራ ነው ብለዋል።

ስልጠናው የፖሊስ አመራሩ እና አባላቱ የሚሰጣቸውን ግዳጅ በብቃት እና በስኬት በመፈጸም የተጀመረውን የህግ ማስከበር ተግባር በውጤታማነት ለማጠናቀቅ የሚያስችል ቁመናን የሚፈጥር መሆኑንም አስረድተዋል።

የፖሊስ ተቋሙን የከፍታ ጉዞ በመረዳት ፍትሐዊ የፖሊስ አገልግሎትን ለህዝብ እንድንሰጥ የሚያስችል እንዲሁም ሀገራችን ያለችበትን የጂኦ ስትራቴጅክ ቁመና ላይ የተሻለ ግንዛቤ አግኝቶ እንደ ፖሊስ የሚጠበቅብንን ተልዕኮ ለመወጣት የሚያስችል ስልጠና መሆኑን ምክትል ኮሚሽነር አበበ ደለለ የአማራ ክልል ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ፕሬዝዳንት እና የስልጠናው አስተባባሪ አጽንኦት ሰጥተው አብራርተዋል።

የአማራ ክልል ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ፣ የምስራቅ ጎጃም ዞን፣ የምዕራብ ጎጃም ዞን እና የደብረ ማርቆስ ከተማ ፖሊስ አመራሮች እና አባላት እንዲሁም የአድማ መከላከል ሻለቃ አዛዦች በስልጠናው እየተሳተፉ ይገኛሉ።

ስልጠናው ለተከታታይ ስድስት ቀናት የሚሰጥ ይሆናል።

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Scroll to Top