የተረጋጋች ሀገር እና ጤናማ ማህበረሰብ ለመገንባት በንጽህና፣ በቁርጠኝነት እና በብቃት የሙስና ወንጀልን መከላከል እንደ ሚገባ ተገለጸ።

የተረጋጋች ሀገር እና ጤናማ ማህበረሰብ ለመገንባት በንጽህና፣ በቁርጠኝነት እና በብቃት የሙስና ወንጀልን መከላከል እንደ ሚገባ ተገለጸ።

‘ትውልድን በስነ-ምግባር ተቋምን በአሰራር እንገንባ’ በሚል መሪ ሀሳብ በአለም ለ22ኛ ጊዜ በኢትዮጵያ ለ21ኛ ጊዜ የሚከበረውን የፀረ-ሙስና ቀን ምክንያት በማድረግ የአማራ ክልል ፍትህ ቢሮ አመራሮችና ሰራተኞች ውይይት አካሂደዋል።

በስልጠና መርሃ-ግብሩ ተገኝተው የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የአማራ ክልል ፍትህ ቢሮ ኃላፊ አቶ ብርሃኑ ጎሽም ሙስና የግለሰቦችን ኪስ የሚያዳጉስ የመንግስትን ኢኮኖሚ የሚያኮስስ ህገ-ወጥ ተግባር በመሆኑ የፍትህ ተቋማት ያለምንም መከፋፈል እና አድሎ አገልግሎት በመስጠት ድርጊቱን መከላከል ይገባል ብለዋል።

እንደ አቶ ብርሃኑ ጎሽም ገለጻ የተረጋጋች ሀገር እና ጤናማ ማህበረሰብ ለመገንባት የፍትህ አካላት በንፅህና፣ በቁርጠኝነት እና በብቃት አገልግሎት መስጠት እንደሚገባቸው ገልጸዋል።

ኢኮኖሚን እየጎተተ እና የማህበረሰቡን ህይወት እያቃወሰ የሚገኘውን የሙስና ወንጀል በስነ-ምግባር ታንጾ መስራት እንደሚገባም አቶ ብርሃኑ ጠቁመዋል።

ተቋማችን ሙስናን ሊያልፈው የማይችለው ቀይ መስመራችን በመሆኑ እራሳችንን ከሙስና አፅድተን ለህዝብ የምንሰጠውን አገልግሎት በማዘመን በታማኝነት በቅንነትና በኃላፊነት መስራት ይኖርበታል ሲሉ አክለዋል።

የወንጀሉን አደገኛነት በመረዳት በየደረጃው የሚገኝ የፍትህ አካል በራስ መተማመን ተግባሩን መከወን ይኖርበታል ብለዋል።

የሙስና ወንጀል ውስብስብ በመሆኑ የፍትህ ተቋማት የህዝብን ግንዛቤ በማሳደግ ከሌሎች አጋር አካላት ጋር በመቀናጀት በሙስና ወንጀል ውስጥ የሚገኙ አካላትን መረጃ እንዲሰጡና ለህግ እንዲቀርቡ ማድረግ የመጀመሪያ ተግባራችን ሊሆን ይገባል ሲሉም አቶ ብርሃኑ አሳስበዋል።

የአማራ ክልል ፍትህ ቢሮ የጸረ-ሙስና ዳይሮክተሬት ዳይሬክተር አቶ ዳኘ አድማሱ በበኩላቸው ሙስና ግለሰቦች ያልተገባ ሀብትን የሚያካብቱበትና ብልሹ አሰራርን የሚያስፋፉበት በመሆኑ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍልና አጋር የፀጥታ አካል ከፍተኛ ርብርብ በማድረግ ልንከላከለው ይገባል ብለዋል።

ስልጣንን አላግባብ መጠቀም፣ ጉቦ መቀበልና መስጠት ለሙስና ወንጀል ተጋላጭነትን የሚጨምሩና የሀገርን ኢኮኖሚ የሚያደቁ በመሆናቸው የፍትህ አካሉ ከህብረተሰቡ ጋር በመቀናጀት መስራት ይኖርባቸዋል ብለዋል።

የአማራ ክልል ፍትህ ቢሮ የፀረ-ሙስና ወንጀል ዳይሮክትሬት የክልል ዐቃቢ ህግ አቶ ፈቃዴ ምስጋናው በበኩላቸው ሙስና በአሁን ሰዓት በክልላችን አገልግሎት በሚሰጡ ተቋማት ፈታኝና ውስብስብ ወንጀል መሆኑን ገልፀዋል።

ከሙስና የፀዳ ፍትሐዊና ግልፅ አሰራርን በማስፈን የፍትህ አካላት ለገቡለት ሙያ በመታመን መስራት ይኖርባቸዋል ብለዋል።

ሙስና የሀገርን እድገት ወደ ኋላ የሚጎትት በማህበረሰቡ ላይ መተማመንን የሚያሳጣ እንዲሁም ለሀገር የሚጠቅም ሀብት ውስን ግለሰቦች የሚያከብር በመሆኑ ልንታገለውና ልናስቀረው ይገባል ሲሉም የውይይቱ ተሳታፊዎች አብራርተዋል።

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Scroll to Top