“የቆምንለት ሀገራዊ ዓላማ፣ የምናስከብረው ብሄራዊ ጥቅምና የምናገለግለው ህዝብ አለን።” ኮሚሽነር ዘላለም መንግስቴ (ዶ/ር)
በወሎና በሸዋ ቀጠና ሲሰጥ የቆየው የጂኦስትቴጂካዊ እና የአመራር አቅም ግንባታ ስልጠና ተጠናቋል።
በማጠቃለያ መርሀ-ግብሩ ላይ በመገኘት የማጠቃለያ ሀሳብና የስራ መመሪያ የሰጡት ኮሚሽነር ዘላለም መንግስቴ (ዶ/ር) የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ “የምናስከብረው ብሄራዊ ጥቅም እና የምናገለግለው ህዝብ አለን” ብለዋል።
እንደ ኮሚሽነር ዘላለም መንግስቴ (ዶ/ር) ገለጻ ለምናገለግለው ህዝብ እና ለገባነው ቃል እንዲሁም ሙያዊ ስነ-ምግባርን የሚመጥን ተግባር መወጣት ይገባል።
የፖሊስ ሰራዊቱ ከአልተገቡ ተግባራት በመራቅ፣ ከክልል የተሻገረ ህብረ-ብሄራዊ አስተሳሰብን በመላበስ ለሙያውና ለሚያገለግለው ህዝብ ዋጋ እና ክብርን ባጎናጸፈ መልኩ ኃላፊነቱን መወጣት አለበት ሲሉም ኮሚሽነር ዘላለም መንግስቴ (ዶ/ር) አሳስበዋል።
አቶ ይርጋ ሲሳይ የአማራ ክልል ብልፅግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ክልሉ ባልተረጋጋ ሁኔታ ውስጥ ሆኖም ፖሊስ ችግሮችን ለመቀልበስ እና ነገን የተሻለ ለማድረግ የሚያስችል ቁመና ላይ ይገኛል ብለዋል።
ክልሉን የሚረብሹ ህገ-ወጥ አካላትን ከህግ ማስከበር ተግባር ጎን ለጎን በህዝብ ግንኙነት ስራ የሰላም አማራጭን እንዲከተሉ ማድረግ ይገባል ሲሉ አቶ ይርጋ ሲሳይ አክለው ተናግረዋል።
የክልሉ ብሎም የሀገሪቱ ህዝብ ሰላም እንዲረጋገጥ ሁሉም አካል መረባረብ እንደሚኖርበትም ጠቁመዋል።
የሰሜን ምስራቅ ዕዝ ዋና አዛዥ ሌተናል ጀኔራል አሰፋ ቸኮል እንደገለጹት እንደ ሀገር ተመሳሳይ ዓላማና ግብ፣ አንድ የጋራ ሀገርና ታሪክ ያለን ነን ሲሉ አንስተዋል።
የሀገራችንን ሰላም የሚያውኩ ህገ-ወጥ አካላትን በጋራ በመመከት በኩል የክልሉ የጸጥታ ኃይል ሚና ጉልህ መሆኑን ሌተናል ጀኔራል አሰፋ ቸኮል በስልጠናው ማጠቃለያ ላይ አብራርተዋል።
የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ ምክትል ኮሚሽነር እና የወንጀል መከላከል ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ምክትል ኮሚሽነር አበበ ውቤ በበኩላቸው ስልጠናው መነቃቃትን የፈጠረ እንዲሁም የተጀመረውን የለውጥ ስራ ተረድቶ ተግባራዊ ለማድረግ ሰራዊቱ ባለቤትነት ተሰምቶት እንዲከውን ያስችለዋል ብለዋል።
ከስልጠናው ያገኘነውን እውቀት ተጠቅመን የክልሉን ህዝብ ሰላም ማረጋገጥ ይኖርብናል ያሉት ምክትል ኮሚሽነር አበበ ውቤ የተጠናከረ የወንጀል መከላከል ስራ ለመስራትም ከህብረተሰቡ ጋር ተቀናጅቶ ተግባራትን መከወን እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
ረዳት ኮሚሽነር የሽወርቅ ላቀው የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ የኮሚሽነር ልዩ ጽህፈት ቤት ኃላፊ በበኩላቸው ተቋሙ ያከናወናቸው የሪፎርም ተግባራት ለፖሊስ ሰራዊቱ የመስራትና የመፈፀም አቅምን የሚያሳድጉ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።
የሚሰጠውን ግዳጅ በብቃት እና በስኬት የሚወጣ ሰራዊት በመገንባት በሀገራችን ጂኦስትቴጂካዊ ቁመና እና ሉዓላዊነት ጉዳይ የማይደራደር እንዲሁም ለሀገር ብሄራዊ ጥቅም ቅድሚያ የሚሰጥ ሰራዊት መሆን ያስፈልጋል ሲሉ አብራርተዋል።
የስልጠና ተሳታፊዎችም ስልጠናው የተቋሙን የከፍታ ዘመን ጉዞ መረዳት የሚያስችልና ለቀጣይ ተግባራት አቅምን በማጎልበትና በሀገራችን ጂኦስትቴጂካዊ ቁመና ላይ የተሻለ ግንዛቤ እንደፈጠረላቸው ገልፀዋል።
ክልላችን ከገጠመው የጸጥታ ችግር ለመውጣት እና ስኬታማ የህግ ማስከበር ስራን ለመከወን የሚያስችል ቁመናን ለመገንባት ስልጠናው አቅም አንደሚሆናቸም ተናግረዋል።
የስልጠናው ተሳታፊ የፖሊስ አመራርና አባላትም በኮምቦልቻ ከተማ አስተዳደርና በደብረብርሃን ከተማ አስተዳደር የሚገኙ የመሰረተ ልማት ስራዎችን እና ፋብሪካዎችን የጎበኙ ሲሆን በስልጠናው ድጋፍ ላበረከቱ አካላትም የእውቅና እና የሽልማት መርሀ-ግብር ተካሂዷል።
በመጨረሻም ሰልጣኞች ባለ ስድስት ነጥብ የአቋም መግለጫ በማውጣት እና ቃለ መሀላቸውን በማደስ ስልጠናው ተጠናቋል።




















