በጎንደር ከተማ የነዳጅ እጥረትን ለግል ጥቅማቸው በሚያውሉ አካላት ላይ የማያዳግም እርምጃ እየተወሰደ መሆኑ ተገለጸ!!

በጎንደር ከተማ የነዳጅ እጥረትን ለግል ጥቅማቸው በሚያውሉ አካላት ላይ የማያዳግም እርምጃ እየተወሰደ መሆኑ ተገለጸ!!

በሀገር አቀፍ ደረጃ የተከሰተውን የነዳጅ አቅርቦት እጥረት ተገን በማድረግ ህገ-ወጥ የነዳጅ ግብይትና የትራንስፖርት ታሪፍ ጭማሪ በሚያደርጉ አካላት ላይ ጥብቅ ቁጥጥርና አስተዳደራዊ እርምጃ እየተወሰደ መሆኑን የጎንደር ከተማ አስተዳደር ፖሊስ መምሪያ አስታወቀ።

የከተማ አስተዳደሩ ፖሊስ መምሪያ አዛዥ ኮማንደር አንተነህ ቴወድሮስ እንደገለጹት የነዳጅ ሀብትን በፍትሐዊነትና በእኩልነት ለማህበረሰቡ ተደራሽ ለማድረግ የተቀናጀ ግብረ-ሀይል ተቋቁሞ ወደ ስራ መግባቱን ጠቁመዋል።

ግብረ-ሀይሉ የነዳጅ ስርጭቱ ሥርዓት እንዲይዝ ግብይቱ ግልጽ እንዲሆንና ህዝቡ ተገቢውን አገልግሎት እንዲያገኝ በከፍተኛ ኃላፊነት እየሰራ እንደሚገኝም አክለዋል።

እንደ ኮማንደር አንተነህ ቴወድሮስ ገለጻ የዞኑ የጸጥታ ኃይል ከግብረ-ኃይሉ ጋር በመቀናጀት በማደያዎች ፣በኬላዎችና የትራፊክ መጨናነቅ በሚታይባቸው አካባቢዎች የሰው ኃይል ስምሪት በማድረግ ህገ-ወጥነትን በንቃት አየተከላከለ ይገኛል ብለዋል።

የግብረ ኃይሉ ስራ በጸጥታ ቁጥጥር ላይ ብቻ የተገደበ አይደለም ያሉት ኮማንደር አንተነህ ቴወድሮስ በከተማዋ አስተማማኝ የነዳጅ አቅርቦትና ፍትሐዊ የንግድ ስርጭት እንዲኖር ለማስቻል ከንግድ ቢሮ ጋር የጋራ ውይይትና ዝርዝር የስራ ስምሪት ተደርጓል ብለዋል።

በንግድ ባለሙያዎችና በጸጥታ አካላት መካከል የተፈጠረው ጠንካራ ቅንጅት የነዳጅ ግብይቱ ከማደያ እስከ ሸማች ባለው ሂደት ውስጥ ህጋዊ መስመሩን ጠብቆ እንዲሄድና ማንኛውም የአቅርቦት ክፍተት ለህገ-ወጥ ነጋዴዎች ዕድል እንዳይሰጥ ለማድረግ ትልቅ ሚና እየተጫወተ እንደሚገኝም አዛዡ አረጋግጠዋል።

ኮማንደር አንተነህ አክለውም ግብረ ኃይሉ ከንግድ ቢሮ በሚገኝ መረጃና የሙያ እገዛ የታገዘ ድንገተኛ ፍተሻዎችን በማካሄድ፣ በንግድ ስርጭቱ ላይ የሚስተዋሉ ማነቆዎችን በዝርዝር እየለየ እርምጃ እየወሰደ መሆኑን አረጋግጠዋል።

የከተማ አስተዳደሩ ፖሊስ ምምሪያ የወንጀል መከላከል ምክትል መምሪያ አዛዥ ኮማንደር ስማቸው አደመ በበኩላቸው ከተቀመጠው የትራንስፖርት ደንብ ውጭ ትርፍ የሚጭኑና ተገቢ ያልሆነ ክፍያ የሚጠይቁ አሽከርካሪዎች ላይ የትራፊክ ፖሊስ ጥብቅ ክትትል እያደረገ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

በማደያዎች በባጃጆችና በኬላዎች ላይ በሚደረግ ድንገተኛ ፍተሻ በጀሪካን የሚቀዳና ለህገ-ወጥ ንግድ የሚውል ነዳጅ በቁጥጥር ስር እየዋለ እንደሆነ ኮማንደር ስማቸው አደመ አረጋግጠዋል።

ለዚህ ማሳያው ደግሞ መጋቢት 24 ቀን 2018 ዓ.ም በተደረገ ድንገተኛ ፍተሻ በህገወጥ መንገድ ለመሸጥ የተካማቸ 332 ሊትር ወይም በ166 ሃይላድ ቤንዚን በህብረተሰቡ ጥቅማ መሰረት የተያዘ መሆኑን አዛዡ ገልጸዋል ።

በቀበሌ10 ሽባበው ቤት በቅንጅት ፍተሻ 232 ሊትር ቤንዚን ተይዟል፤ እንዲሁም በቀበሌ15 አሸናፊ የተባለ ግለሰብ ጅምር ህንፃ ላይ 100 ሊትር ቤንዚን መያዙን አረጋግጠዋል።

ኮማንደር ስማቸው አደመ አክለውም ባለፉት ሁለት ሳምንታት ውስጥ ብቻ በተከናወነ የተቀናጀ ኦፕሬሽን አስደናቂ ውጤቶች መመዝገባቸውን የጠቀሱት አዛዡ ትርፍ በመጫን፣ ከታሪፍ በላይ በማስከፈልና ህገ-ወጥ ነዳጅ በማዘዋወር የተሳተፉ 1,770 ተሽከርካሪዎች የተያዙ ሲሆን፣ በአጠቃላይ 2 ሚሊዮን 159 ሺህ ብር ቅጣት ተጥሎ ለመንግስት ገቢ መኆኑንም አክለዋል።

ለሕዝብ አገልግሎት ቅድሚያ የሚሰጣቸው ተሽከርካሪዎች ያለምንም እንግልት ነዳጅ አግኝተው ስራቸውን እንዲሰሩ ተደርጓል።

ነዳጅ በመደበቅ ፣ ለደላላ አሳልፎ በመስጠትና ለህገ-ወጥ ንግድ ተባባሪ በመሆን ህዝብን የሚያማርሩ ማደያዎችም ሆኑ በድርጊቱ የሚሳተፉ አካላት ላይ የማያዳግም እርምጃ እየተወሰደ እንደሚገኝም ጠቁመዋል።

በኬላዎች ላይ የሚደረገው ፍተሻ ተጠናክሮ መቀጠሉንና በአቋራጭ ለመክበር የሚሹ አካላትን ሰላም የመንሳት ተግባር ፖሊስ እንደማይታገሰውም አረጋግጠዋል።

ማህበረሰቡ እያሳየ ያለው ጥቆማ የመስጠትና ከጸጥታ ኃይሉ ጎን የመቆም ባህል የሚደነቅ መሆኑን ገልጸው የጸጥታ ግብረ-ኃይሉ የጀመረውን ህገ-ወጥ ተግባር የመከላከል ስራ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ኮማንደር ስማቸው አደመ አረጋግጠዋል።

በክልሉ እስካሁን ከ90 ሺህ በላይ ሕገ ወጥ ነጋዴዎች ላይ እርምጃ የተወሰደባቸው ሲሆን በሕገ ወጥ መንገድ ለግብይት ሊቀርብ የነበረን 300 ሺህ ሊትር ናፍጣ፣ 155 ሺህ 363 ሊትር ቤንዚን በድንገተኛ ፍተሻ በቁጥጥር ስር የዋለ ሲሆን በገንዘብ ሲተመንም 55 ሚሊዮን ብር እንደሚሆን መረጃዎች ይጠቁማሉ።

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Scroll to Top