የጸጥታና ደኅንነት ተቋማት የሰላም ጋሻ፣ የብሔራዊ ክብርና ጥቅማችን ዘብ ናቸው።
‘የጸጥታና ደኅንነት ተቋማት ቅንጅት ለሀገራዊ ሰላም እና ደኅንነት’ በሚል መሪ ቃል የተካሄደው ብሔራዊ የደኅንነት ኮንፍረንስ በዛሬው ዕለት ተካሂዷል።
በኮንፍረንሱ ላይ የሀገሪቱን ወቅታዊ የሰላም ሁኔታና የቀጣይ የትኩረት አቅጣጫዎችን የተመለከቱ ዝርዝር ጉዳዮች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል።
በመድረኩ ላይ እንደተመለከተው፣ ኢትዮጵያ በቀጣናው የሚስተዋሉ የእርስ በእርስ ጦርነቶችን፣ የአሸባሪ ቡድኖችን ሴራ እና የመካከለኛው ምስራቅ ጂኦ-ፖለቲካዊ ውጥረቶችን በጽናት ተቋቁማ ማለፍ ችላለች። ይህም ሊሆን የቻለው በጸጥታና ደኅንነት ተቋማት ጥንካሬና በልጆቿ መስዋዕትነት መሆኑ ተመላክቷል።
የሪፎርም ውጤቶችና የቴክኖሎጂ ሽግግር ባለፉት የለውጥ ዓመታት የተከናወኑ የሪፎርም ሥራዎች ተቋማቱ ችግሮችን ወደ ዕድል እንዲቀይሩ ማስቻላቸው ተገልጿል።
በተለይም ተቋማቱ በቴክኖሎጂ፣ በሰው ኃይልና በአደረጃጀት ዘመናዊ መሆናቸው፣ ከሕዝብ አጋርነት ጋር ተዳምሮ ለሀገራዊ ሁለንተናዊ ውጤት መመዝገብ ትልቅ ድርሻ ማበርከቱ ተጠቁሟል።
በኦሮሚያና በአማራ ክልሎች ሰላምን ለማስፈን የተሄደባቸው ርቀቶችና የተገኙት ውጤቶች የሚበረታቱ መሆናቸው የተገለጸ ሲሆን፣ በመላ ሀገሪቱ አስተማማኝ ሰላም እስኪሰፍን ድረስ የጸጥታ ተቋማትና የሕዝቡ የተቀናጀ ርብርብ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተረጋግጧል።
በመጪው ግንቦት ወር መጨረሻ የሚካሄደው 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ሰላማዊ እና ዴሞክራሲን የሚጸናበት ታሪካዊ ምዕራፍ እንዲሆን የጸጥታ ተቋማት ኃላፊነታቸውን በቁርጠኝነት እንደሚወጡ እምነት ተጥሎባቸዋል።
ኮሚሽነር ጀኔራል ዘላለም መንግስቴ (ዶ/ር) የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና አዛዥ ይህንኑ ወሳኝ የፓናል ውይይት በሞደሬተርነት (አመቻችነት) እየተሳተፉ ይገኛሉ።
በውይይቱ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህን ጨምሮ የፌዴራልና የክልል ከፍተኛ የጸጥታ አመራሮች፣ የደኅንነት ተቋማት የስራ ኃላፊዎችና የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል
በመጨረሻም ለሀገር ህልውና መስዋዕትነት ለከፈሉና ሌት ተቀን ለሚተጉ የጸጥታና ደኅንነት አመራሮችና አባላት፣ እንዲሁም ለኢትዮጵያ ሕዝብ ጥልቅ አክብሮት ተገልጾ፤ ለነገው ትውልድ የምትመጥን ሀገር ለመገንባት በሚደረገው ጉዞ የዓላማ ጽናት አስፈላጊ መሆኑ ተመልክቷል።






