የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ የ500 ሺህ ዩሮ ዋጋ ግምት ያላቸው ዘመናዊ የፎረንሲክ ላብራቶሪ መሳሪያዎችን ከአውሮፓ ህብረት በድጋፍ አገኘ
የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ የ500 ሺህ ዩሮ ዋጋ ግምት ያላቸው ዘመናዊ የፎረንሲክ ላብራቶሪ መሳሪያዎችን ከአውሮፓ ህብረት በድጋፍ አግኝቷል።
ዘመናዊ የፎረንሲክ ላብራቶሪ መሳሪያዎቹን ለክቡር ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል ያስረከቡት በኢትዮጵያ የአውሮፓ ህብረት አምባሳደር ክብርት ሶፊ ፍሮም-ኤመስበርገር ናቸው።
ክቡር የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል በርክብክብ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ ባደረጉት ንግግር ድጋፉ ኢትዮጵያ የፍትህ እና የህግ አስከባሪ ተቋማትን የበለጠ ውጤታማ እና ቀልጣፋ ለማድረግ በትጋት እያሰራችበት ባለችበት ወቅት መሆኑ ልዩ ያደርገዋል ብለዋል።
ክቡር ኮሚሽነር ጀነራል አያይዘውም በድጋፍ የተገኙት ዘመናዊ የፎረንሲክ መሣሪያዎች ሳይንሳዊ ምርመራዎች፣ የወንጀል ስፍራ ትንተና፣ የጣት አሻራ መለያ፣ የጦር መሳሪያ መረጃ ትንተና እና የክትትል ማስረጃዎችን መመርመር የሚያስችሉ መሆናቸውን ገልፀው እያንዳንዱ የላብራቶሪ መሣሪያ የሕዝብ ደህንነትን ለመጠበቅ እና የህግ የበላይነትን ለማስከበር ድርሻው ከፍ ያለ ነው ብለዋል።
ክቡር ኮሚሽነር ጀነራል በዛሬው ዕለት የተደረገው ድጋፍ የፍትህ ሥርዓታችንን የሚያሳድጉና መንግሥታችን እያደረገ ያለውን የፀጥታ ዘርፍ ማሻሻያ ኢኒሼቲቭ (Security Sector Reform Initiative) ለማሳካት የላቀ አስተዋጽኦ አለው ብለዋል።
ዘመናዊ የፎረንሲክ ላብራቶሪ መሣሪያዎቹ ትክክለኛ፣ ወቅታዊ እና ተአማኒ የሆኑ ምርመራዎችን ለማካሄድ፣ ፍትሃዊ የፍርድ ሂደትን ለማረጋገጥ እና የዜጎቻችንን ሰብዓዊ መብቶች ለማስጠበቅ መሰረት እንደሆኑም ጨምረው ገልፀዋል።
ዘመናዊ የፎረንሲክ መሣሪያዎቹ አሠራራችን በማሻሻል ለምናገለግለው ኅብረተሰብ ትልቅ ትርጉም ያላቸው እና ዘላቂ ተጽእኖ የሚያሳድሩ በመሆናቸው የወንጀል ምርመራ አመራር እና ባለሙያዎች በዕለት ተዕለት ተግባር ውስጥ የምትጠቀሙባቸውን እነዚህን መሳሪያዎች በአግባቡ እንዲይዙ አሳስበዋል።
ክቡር ኮሚሽነር ጀነራል የአውሮፓ ህብረት ላደረገው ዘመናዊ የፎረንሲ ላብራቶሪ መሳሪያዎች ድጋፍ በኢትዮጵያ መንግስት እና በኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ስም ላቅ ያለ ምስጋና አቅርበዋል።
በኢትዮጵያ የአውሮፓ ህብረት ክብርት አምባሳደር ሶፊ ፍሮም-ኤመስበርገር በበኩላቸው እነዚህ ዛሬ የለገስናቸው ዘመናዊ የፎረንሲክ መሳሪዎች በአውሮፓ ህብረት የወንጀል ፍትህ ድጋፍ ማሻሻያ ፕሮግራም ማዕቀፍ ውስጥ የቀረቡ ልዩ የፎረንሲክ መሳሪያዎችን ለኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ በማስረከቤ ከፍተኛ ደስታ ተሰምቶኛል ብለዋል።
የፎረንሲክ ምርመራ አቅምን በመደገፍ፣ የአውሮፓ ህብረት በሀገር አቀፍ ደረጃ የፖሊስን ውጤታማነት፣ ተአማኒነት እና ግልፀኝነት ላይ ኢንቨስት እንደሚያደርግ የተናገሩት ክብርት አምባሳደር ድጋፉ የህግ አስከባሪ ተቋማትን ለማጠናከር እና የህዝብ አመኔታን ለመገንባት በማሰብ በወንጀል ፍትህ ሰንሰለት ውስጥ የተደረጉ ማሻሻያዎችን ለመደገፍ ከሚደረገው ሰፊ የአውሮፓ ህብረት ጥረት አንዱ አካል መሆኑን ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ የሕግ የበላይነትን ለማጠናከር እና ተጠያቂነትን ለማረጋገጥ የምታደርገውን ጥረት አጠናክራ እንድትቀጥል የአውሮፓ ህብረት አስተማማኝ አጋር ሆኖ እንደሚቀጥል አምባሳደር ሶፊ ፍሮም-ኤመስበርገር መግለጻቸውን የፌዴራል ፖሊስ አስታውቋል።












