የማህበረሰብ ዓቀፍ ወንጀል መከላከል ስራ ወንጀልን በመከላከል ከተሳታፊነት ወደ ባለቤትነት የተሻገረ ማህበረሰብ የተፈጠረበት አሰራር መሆኑ ተገለፀ።

የማህበረሰብ ዓቀፍ ወንጀል መከላከል ስራ ወንጀልን በመከላከል ከተሳታፊነት ወደ ባለቤትነት የተሻገረ ማህበረሰብ የተፈጠረበት አሰራር መሆኑ ተገለፀ።

በኮምቦልቻ ከተማ አስተዳደር በማህበረሰብ ዓቀፍ ወንጀል መከላከል ተግባር በከተማዋ የሚፈፀሙ ወንጀሎችን ለመከላከልና ለመቆጣጠር በሚደረጉ ተግባራት ከፀጥታ ሀይሉ ጎን ለጎን የከተማዋ ማህበረሰብ ከተሳታፊነት ባለፈ በባለቤትነት ስሜት ትልቅ ኃላፊነትን እየተወጣ እንደሚገኝ የከተማ አስተዳደሩ ፖሊስ መምሪያ የማህበረሰብ ዓቀፍ ወንጀል መከላከል ዋና ክፍል ኃላፊ ኮማንደር ንጋቱ ታመነ ተናግሩ።

የከተማው ማህበረሰብ ወንጀልን እና ወንጀለኛን አምርሮ የሚጠላ በመሆኑ ከከተማው የፀጥታ ሀይል ጋር በመቀናጀት ወንጀልን አስቀድሞ በመከላከልና ወንጀል ተፈፅሞ ሲገኝ ጥቆማና መረጃ በመስጠት ውጤታማ ስራዎች እየተከናወኑ እንደሚገኙም ኮማንደር ንጋቱ ታመነ ገልፀዋል።

የፖሊስ ተቀዳሚ ተግባር ወንጀልን መከላከል ነው ያሉት ኃላፊው በከተማው ውስጥ የተለያዩ የወንጀል ድርጊቶች እንዳይፈፀሙ የአከራይ ተከራይ ውል፣የቤት ለቤት ፍተሻ፣ሰርጎ ገብነትን መቆጣጠር እና መሰል የቅድመ ወንጀል መከላከል ስራዎች እየተሰሩ ነው ብለዋል።

የከተማችንንና የማህበረሰባችንን ሰላም ለማስጠበቅ የፖሊስ ኀይላችን ከማህበረሰቡ ጋር በመሆን ከቀን የፍተሻ ስራ በተጨማሪ በምሽትም የስጋት አካባቢን በመለየትና የቅኝት ስራን በማጠናከር ወንጀልን እየተከላከልን እንገኛለን ያሉት ደግሞ ምክትል ኢንስፔክተር አንዋር ሰይድ የኮምቦልቻ ከተማ አስተዳደር ፖሊስ መምሪያ የቦርከና ክፍለ ከተማ የማህበረሰብ ዓቀፍ ወንጀል መከላከል ክፍል ኃላፊ ናቸው።

በወንጀል መከላከል ስራ ፖሊስ ያለማህበረሰቡ ድጋፍ ብቻውን ውጤት ማምጣት አይቻልም ያሉት ምክትል ኢንስፔክተር አንዋር ሰይድ የማህበረሰብ ዓቀፍ የወንጀል መከላከል ስራ ማህበረሰቡን ባለቤት የሚያደርግ አሰራር በመሆኑ ውጤቱ የላቀ ነው ሲሉም ገልፀዋል።

በምሽት አካባቢያቸውን ሲጠብቁ ካገኘናቸው የማህበረሰብ ክፍሎች መካከል አቶ አያልነህ አሸናፊ ከከተማችን ፖሊስ ጋር በመቀናጀት ወንጀልን ለመከላከል የስጋት ቀጠናዎችን በመለየት የጥበቃና የቅኝት ስራ በመስራት የተለያዩ የስርቆት፣የዝርፊያና የእገታ ወንጀሎችን እንዲቀንሱ ማድረጋቸውን ገልፀዋል።

ሌላኛው አካባቢያቸውን ከወንጀል ለመከላከል በምሽት ሲጠብቁ ያገኘናቸው አቶ ይመር ዳውድ በበኩላቸው ፖሊስ ለወንጀል መከላከል ስራ መሪና አመላካች እንጂ ብቻውን ውጤታማ ስለማይሆን ሁሉም ማህበረሰብ አካባቢውን በመጠበቅና ለፀጥታ ሀይሉ አይንና ጆሮ በመሆን ወንጀልን ማስቀረት እንደሚገባም ጠቁመዋል።

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Scroll to Top