ራሱን የጎቤ ክፍለ ጦር ሰጠኝ ባብል ብርጌድ ብሎ የሚጠራው ታጣቂ ቡድን የሰላም ጥሪውን ተቀብሎ እጅ መስጠቱ ተገለጸ።
በማዕከላዊ ጎንደር ዞን በማዕከላዊ አርማጭሆ ወረዳ በሚገኙ የተለያዩ ቀበሌዎች ታጥቆ ሲንቀሳቀስ የነበረው ራሱን የጎቤ ክፍለ ጦር ሰጠኝ ባብል ብርጌድ ብሎ የሚጠራው በጌታለ የማታው የሚመራው ህገ-ወጥ ታጣቂ ቡድን የሰላም ጥሪውን ተቀብሎ ዘጠኝ የቡድን አባላቱን በመያዝ ለመንግስት እጅ መስጠቱን የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ፖሊስ መምሪያ አስታውቋል።
ህገ-ወጥ ታጣቂ ቡድኑ ሲገባ አንድ ዲሽቃ፣ አንድ አርባ ጎራሽ እና አምስት ክላሽ መሣሪያ እንዲሁም አባላቱ እስከነ ሙሉ ትጥቃቸው በሰላማዊ መንገድ ለመንግስት እጅ ሰጥተዋል።
የቡድኑ መሪ አቶ ጌታለ የማታው መንግስት የህዝባችን ጥያቄዎች የሚፈታ ከሆነ እኛም ከመንግስት እና ከህዝብ ጎን በመሰለፍ ሌሎች ጫካ የሚኖሩ ወንድሞቻችን ወደ ሰላም የሚመጡበት ሁኔታ ለማመቻቸት ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል።
መንግስት ያስተላለፈውን የሰላም ጥሪ ተከትሎ በርካታ ህገ-ወጥ ታጣቂዎች በሰላም እጃቸውን ለመንግስት እየሰጡ ይገኛሉ።
በልዩ ልዩ ምክኒያት በህገ-ወጥ መንገድ በጫካ የምትንቀሳቀሱ ሌሎች ታጣቂ ቡድኖችም የሰላም አማራጭን በመቀበል ለህዝብ ሰላም እና ደኅንነት ሰላማዊ እንቅስቃሴን እንድትመርጡ በድጋሜ ጥሪ ቀርቦላችኋል።



